በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፣
ነገር ግን እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁና አይዞአችሁ። ዮሐንስ 16:33
ክርስቲያን ነኝ፣ ጌታ በኢየሱስ
ክርስቶስን ተቀብያለሁ፣ የዘለዓለምን ሕይወት በእግዚአብሔር ምህረትና ጸጋ አግኝቻለሁ፣ በልቤ ውስጥ የዘለዓለም ደስታ አለኝ፣ ነፍሴም
ከዘለዓለም ስጋት አርፋለች፣ አንድ ቀን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ እንደሚመጣና ወደ ዘለዓለም ክብር እንደምገባ አምናለሁ። ነገር
ግን በዚያ ታላቅ ተስፋና በዛሬው ኑሮዬ መካከል ያለው ቀን ረዘመ፣ መንገዱ ቀላል አይደለም፣ ፈተናም ይበዛብኛል የምንል ብዙ ነን።
መዝሙረ ዳዊት 34;19
አንዳንዶቻችን የምንወደው እና አለኝ የምንለው ሰው በድንገት በሞት ተለይቶን ሃዘን ሰብሮናል። ሌሎቻችን ህመም ሰውነታችንን ጎድቶት
ስጋችን ሌትና ቀን ከነፍሳችን ጋር እየተሟገች እንሰቃያለን። አንዳንዶቻችን በስደት ምድር በመንከራተትና ከብቸኝነት ጋር በትንቅንቅ
ውለን ስናድር ሌሎቻችን ደግሞ በከባድ በሽታ የታመመን ዘመድ፣ ልጅ፣
የትዳር ባልንጀራ ወይም ጓደኛ ስቃይ እያየንና እነርሱንም ለመርዳት ስንታገል ልባችን ዝሎአል። አንዳንዶቻችን ጌታን ስላመንን ብቻ
በወህኒ ተጥለን እንሰቃያለን። ሌሎቻችን ደግሞ ይህ ሁሉ ባይደርስብንም እንኳን የኑሮን አንድ ጫፍ ከሌላው ለማገናኘት ሌትና ቀን
ብንሰራም ጠብ አልል እያለን እንመረራለን፣ ከአለቆቻችን እና ከስራ ባልደረቦቻችን በሚደርስብን በደል አንገታችንን ደፍተን እንመላለሳለን።
አንዳንዶቻችን ያመንነው ሰው ክዶን ልባችን ተሰብሮአል፣ ሌሎቻችን ተስፋ ያደረግነውና ብዙ የደከምንለት ነገር አልሳካ ብሎን ነፍሳችን
ዝላለች።
ብዙ ስብከት ሰምተናል እንሰማለንም።
ወደ ጌታ አይናችንን አድርገን አምላኬ ሆይ መቼ ይሆን ይህስ የሚያልፈው እያልን እንጮሃለን። አንዳንድ ጊዜ ሰማይ ነሃስ ምድርም
ብረት የሆነችብን ይመስለናል። አንዳንዶቻችን ፈተናዎቻችንን ዋጥ አድርገን እንጓዛለን። ሲበዛብንም ለብቻችን አለቃቅሰን እንጸልይና
እንባችንን ጥርግርግ አድርገን እንደ እንደሱነማዊቱ ሴት (2ኛ ነገስት 4:26) ሁሉም መልካም ብለን የጌታን ፊት ብቻ እንጠብቃለን።
ሌሎቻችን ደግሞ አሉን ለምንላቸው ወገኖች ሸክማችንን በማካፈል እንጸልያለን፣
ጸልዩልንም እንላለን። የመከራችን ቀኑ ሲረዝምና ሸክሙ ሲከብድ ተስፋ ወደመቁረጥ የምንቃረብበትም ጊዜ አለ። በመንፈሳዊ ህይወታችን
ጠንካራ ነን ብለን የምናስብ እንኳን ሳንቀር በድል ማግስት በሚገጥመን ፈተና እንደ ኤልያስ ተስፋ በመቁረጥ ከአባቶቼ አልበልጥምና
ነፍሴን ውሰድ እንላለን።
ጌታ እግዚአብሔር ታዲያ
ይህንን ሁሉ ስለሚያውቅ እኮ ነው በባሪያው በዳዊት አፍ እግዚአብሔር አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው (መዝሙር 33፡12)
ብሎ የተናገረው። የእኛ ሊቀካህን ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢዓት በቀር በነገር ሁሉ የተፈተነና ድል ያደረገ ጌታ ነው። ዕብራውያን
4:15። ህመማችን ይሰማዋል እሱም ጀርባው በጅራፍ ተተልትሎ፣ ራሱ በእሾህ አክሊል ቆስሎ፣ እጅና እግሩ በችንካር ጎኑ ደግሞ በጦር
ተወግቶ ነበርና። ረሃብና ጥማታችን፣ መሰደድና መቸገራችን፣ ማዘንና መንከራተታችን ይገባዋል። እሱም በመስቀል ላይ ተጠምቶ ነበርና።
ምናልባት ጌታ አምላክ የሁሉ ባለቤትና ሁሉን ቻይ ስለሆነ ችላ ይለኝ ይሆን ብለን ከፈራን አንድ ገጠመኝ ላካፍላችሁ። በአዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርሁበት ጊዜ፣ አንድ ቀን በጣም ከፍቶኝ ወደ
ዘመድ ቤት በእግሬ ስሄድ በአራዳ ጊዮርጊስ አጠገብ አልፍ ነበር። አንድ ሽማግሌና ዓይነ ስውር የኔ ብጤ ሰው በቤተ ክርስቲያኑ የግንብ
አጥር ስር ተቀምጠው በዜማ ይለምኑ ነበር። ወሩ ነሐሴ ነበርና ዝናብ
ችፍ ችፍ ይል ስለነበር ይበርዳል። የለበሱት አሮጌ ጋቢም በከፊል
በስብሷል። ታዲያ እኒያ አዛውንት የኔ ብጤ ሲለምኑበት ከነበረው ዜማ መካከል አንዱ ስንኝ ጆሮዬ ውስጥ ጥልቅ አለና ከነበርሁበት
ትካዜ ውስጥ አነቃኝ። ያ ስንኝ እስከ ዛሬ ድረስ በልቤ ውስጥ ተቀምጦ የአምላኬን ቅርብነት ያስታውሰኛል። ያ ስንኝ እንዲህ የሚል
ነበር። “አብን ተወውና ንገረው ለወልድ፣ ተሰቅሎአል ተወግሮአል እሱ ያውቃል ፍርድ።” የራሴን ትካዜ ትቼና ከእኒያ የኔ ብጤ የሰማሁትን
አስደናቂ ትምህርት እያሰላሰልሁ ለብዙ ወራት ተጽናናሁ። ወገኖቼ በመከራችን ሁሉ የሚራራልን፣ በጨለማችን ውስጥ ከኛ ጋር የሚጓዝና
እና ጽዋውም ሲሞላ ለዘለዓለም የሚያሳርፈን ጌታ አምላክ አለንና አይዞን። የዘገየ ቢመስልም በእርግጥ ይመጣልና፣ መጥቶም ያድነናልና
እንደምንም ብለን የደከሙ የመንፈስ እጆቻችንን እናበርታ፣ የላሉ ጎልበቶቻችንንም እናጽና። ልቅሶ ማታ ይመጣል፣ ጠዋት ግን ደስታ
ይሆናል። መዝሙር 30 ቁጥር 5። በጌታ ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ