ክፍል አንድ
(ከጽሁፉ መጨረሻ ላይ የተሰጠውን የድረገጽ ማገናኛ በመጫን የተያያዘውን ዜና አንብቡ)
ከ2012 መጨረሻ አካባቢ
ጀምሮ ዓለማችን ከቀዝቃዛው ጦርነት ፍጻሜ በኋላ ገብታ ወደማታውቅበት ከፍተኛ የጦርነት አደጋ ውስጥ ገብታለች። ብዙዎቻችሁ እንደምታስታውሱት
በ2014 እኤአ በዩክሬን የነበረው በህዝብ የተመረጠ መንግስት በምእራባውያን
(በተለይም አሜሪካ) ግፊትና እነሱም ለተቃዋሚዎች በሰጡት ድጋፍ ምክንያት ተገለበጠ። በዚያኑ አካባቢ ነበር የአረብ ስፕሪንግ ስም
የተሰጠውና ለብዙ ዘመናት በስልጣን ላይ የቆዩ የተለያዩ የዓረብ አገሮች መንግስታት ተራ በተራ ይገለበጡ የነበረው። ለምሳሌ የግብጹ
ሆስኒ ሙባረክ፣ የሊቢያው ሙአመር ጋዳፊ እና የቱኒሲያው ፕሬዝደንት ቤን አሊ መገልበጥ አይዘነጋም። በጊዜው በሰፊው ይናፈስ የነበረው ዜና እነዚህ የመንግስት ግልበጣዎች የአገሮቹ ህዝቦች ያመጡአቸው
አብዮቶች ውጤት እንደነበር ቢሆንም ከዚያ በኋላ የወጡ ብዙ መረጃዎች ግን ያ የአረብ ስፕሪንግ ይባል የነበረው አሁንም አንዳንድ
የምእራባውያን አገሮች የማይፈልጓቸውን መንግስታት ከስልጣን ለማስወገድ የወጠኑት እቅድ አካል እንደሆነ ያስረዳሉ። በተለይ ደግሞ
በሊቢያ የተደረገው የመንግስት ግልበጣ ምእራባውያንና አጋሮቻቸው በቀጥታ የተሳተፉበት እንገነበር ግልጽ ነው። ታዲያ ያንን የአረብ
ስፕሪንግ የተባለውን መንግስታትን የመገልበጥና የአገሮችን አስተዳደር በአሜሪካና በአጋሮቿ መልክ ለመቅረጽ እየተለኮሰ የነበረውን
ሰደድ እሳት ወደ ዩክሬን እና ሶሪያ ለማስፋፋት በሚሞከርበት ጊዜ በታላላቆቹ የዓለም የጦር ኃይል ባለቤቶች ማለትም አሜሪካና አጋሮቿ
በአንድ በኩል እና በሌሎች ታላላቅ አገሮች፣ በተለይም በሩሲያ መካከል
ብዙ ውጥረት መፈጠር ጀመረ። ሶቪየት ህብረት በፈራረሰ ጊዜ ሩሲያ እንደገና ተነስታ ምእራቡን ዓለም ልትገዳደር አትችልም የሚል እምነት
አድሮባቸው የነበሩ ምእራባውያን መንግስታት ዲሞክራሲን ለማስፋፋት በሚል ሽፋን የማይፈልጓቸውን መንግስታትን የመቀያየርና አገሮችንም
አፈራርሶ አዳዲሶችን የመመስረት ዓላማቸውን ቀድሞ የሶቪየት ህብረት አካል በነበሩትና በሶቪየት ህብረት ጥላ ስር በነበሩ የምስራቅ
አውሮፓና ሌሎችም ከሩሲያ ጋር የቅርብ ግንኙነት ወዳላቸው አገሮች ማስፋፋት ከጀመሩ ውሎ አድሮአል። የዩጎዝላቪያ መፈራረስ፣ በተለይም
ደግሞ የሰርቢያ ታሪካዊ አካል የነበረችው የኮሶቮ በምእራባውያን ግፊት መገንጠል፣ በዩክሬን እና በጆርጂያ የተደረጉ የቀለም አብዮቶች
ሩሲያን እጅግ አስቆጥተዋል። እንዲሁም ደግሞ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን አከተመ በተባለበት ጊዜ በሶቪየት ህብረት ሲመራ የነበረው
WARSAW የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ሲፈርስ ምዕራባውያን መርተውት የነበረው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO)
ግን በመፍረስ ፈንታ የበለጠ እየተስፋፋ እና ይባሱኑ ደግሞ ቀደም ሲል የሶቪየት ህብረት አካል እና በሶቪየት ህብረት ጥላ ስር የነበሩ
አገሮችን አባል በማድረግ ግዛቱን ወደ ሩሲያ ድንበር እጅግ እያስጠጋ መጣ። ይህ ነገር ያሰጋትና ያሰለቻት ሩሲያ በሶቪየት ህብረት
መፍረስ ተዳክሞ የነበረውን የጦር ኃይሏን ባልተጠበቀ ፍጥነት ዘመናዊ ካደረገችና ካጠናከረች በኋላ አሜሪካንና አጋሮቿን አሁንስ በዛ
ያለች ይመስል በዩክሬን ምእራባውያን የደገፉት የመንግስት ግልበጣ ሲደረግ፣ ለረጅም ዘመናት የሩሲያ አካል የነበረውንና በሶቪየት
ህብረት ዘመን ወደ ዩክሬን ተደባልቆ የነበረውን የክራይሜያን ግዛት ወደራሷ ደባለቀች። እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን የዛሬዋ ዩክሬንም
የሶቪየት ህብረት አካል እንደነበረች ነው። የምእራባውያኑም እቅድ ዩክሬንን ደረጃ በደረጃ የአውሮፓ የጋራ ገበያ እና የሰሜኑ አትላንቲክ
የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አባል በማድረግና ኃይላቸውን በቀጥታ በሩሲያ ድንበር ላይ በማስፈር ሩሲያ በጥቁር ባህር ላይ
ያላትን ታላቅ የጦር ኃይል በማምከን እና አገሪቱ ከጥቁር ባህር ወደ ሜዲትራኒያን ባህር የምትተላለፍበትን መንገድ በራሳቸው ኃይል
በመክበብ ሩሲያ በዓለም ላይ ያላትን ስትራቴጂያዊ ኃይል ለማዳከም መሆኑ ጉዳዩን በቅርብ ለሚከታተሉ ሁሉ ግልጽ ነው። ይህ ያስቆጣት
ሩሲያም ሳልቀደም ልቅደም በማለት በሶቪየት ህብረት ዘመን ከሩሲያ ግዛት ስር ተከፍሎ ወደዩክሬን ገብቶ የነበረውን የክራይሜያን ክልል
ወደራሷ በመደባለቅ የምዕራባውያኑን ሙከራ አመከነች። የቀድሞ የሶቪየት ህብረት ፕሬዝዳንት የነበሩት ጎርባቼቭ ዓለም ለጦርነት እየተዘጋጀች ይመስላል አሉ
ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ ክፍል 2 ከታች ይቀጥላል
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ