ታላላቆቹ የምድር መንግስታት ሳይወዱት በግድ ወደ ጦርነት እየተገፉ ነው።ለምድር መሪዎች እንጸልይ።

ለምድር ታላላቅ አገሮች መሪዎች እንጸልይ። ታላላቆቹ የምድር መንግስታት ሳይወዱት በግድ ወደ ጦርነት እየተገፉ ይመስላል። ባለፉት አስር ቀናት ዓለም ከመቼውም በበለጠ ወደከፍተኛ ጦርነት እየተቃረበች መሆኑን ጉዳዩን በቅርቡ የሚከታተሉ ሁሉ ያስረዳሉ። አሜሪካ TRIDENT የሚባሉ የኑክሊየር ቦምብ ተሸካሚ ሚሳኤሎችን በFLORIDA አካባቢ በቅርቡ ፈተሸች። በነዚሁም ቀናት የሩሲያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ድሚትሪ ሮጎዚን የሩሲያ ዘመናዊ ሚሳኤሎች የአሜሪካንን የሚሳኤል መከላከያ በጣጥሰው ያልፋሉ ብለው ተናገሩ። የሩሲያ የስለላ መርከብ በአሜሪካ ምስራቃዊ ድንበር በባህሩ ላይ ስትሰልል መሰንበቷን በተመለከተ አዲሱ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ሲናገሩ “ለፖለቲካችን ጥሩ የሚሆነው ይችን የሩሲያ መርከብ ከውሃው ላይ መትቼ ማጥፋት ነው። ይህ ግን የኑክሊየር እልቂትን ያመጣል” ብለው የተናገሩትም ባለፈው ሳምንት ነው። በዚህ ባካፈልኳችሁ ዜና ላይ እንደምታዩት ደግሞ የሩሲያው የመከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ 96 ከመቶ የሚሆኑት የሩሲያ የኑክሊየር ሚሳኤሎች በሙሉ ለመተኮስ ዝግጁ ናቸው የሚል ዘገባን ለሩሲያ ምክር ቤት አባላት አቅርበዋል። የእነዚህ ዜናዎች ለዓለም ሁሉ መለቀቅ ዓላማው ዜናውን ለተራው ህዝብ ለማድረስ ሳይሆን፣ ባላንጣዎቻቸውን ለማስጠንቀቅ ነው። አሜሪካና አጋሮቿም በሩሲያ ድንበር እጅግ ቀርበው በሚገኙ የኖርዌክ፣ የፖላንድ፣ የላትቪያ፣ የሊትዌኒያ እና የኢስቶኒያ ከተሞች እንዲሁም ደብሞ በሮማኒያ፣ በቡልጋሪያና ሌሎችም የምስራቅ አውሮፓ አገሮች ከባድ የጦር መሳሪያዎችንና በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወታደሮችን እያሰፈረች ነው። ምእራባውያኑ ከቻይና፣ ከሰሜን ኮሪያና ከኢራን ጋር የገቡበት ውጥረትም በጣም እየከረረ መጥቷል። ባላፈው ሳምንት አሜሪካ የጦር አውሮፕላን እና ሚሳኤል ተሸካሚ መርከቦችን በደቡብ ቻይና ባህር እና በቀይ ባህር በሚገኘው በባብ ኤል መንደብ አካባቢ በማሰማራት ለጦርነት እየተዘጋጀች ይመስላል። ባለፈው እንደጻፍሁት፣ አይበለው እንጂ ጦርነት በተለይ በሩሲያና በአሜሪካ እንዲሁም በአሜሪካና በቻይና መካከል ከተነሳ የሰው ልጅ ከዚህ በፊት አይቶት የማያውቀው እልቂት ሊፈጠር እንደሚችል አያጠራጥርም። ከኢራንና ከሰሜን ኮሪያ ጋርም አሜሪካና አጋሮቿ ጦርነትን ቢያስነሱ የሚፈጠረው ጥፋት ትንሽ አይሆንም።
ከጌታ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን እቅድ በቅርብ የተማረው ሃዋርያው ጴጥሮስ በ2ኛው መልእክቱ ምእራፍ 3 ቁጥር 10 ላይ እንዲህ ይላል: “የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል። በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምጽ ያልፋሉ፣ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኩሳት ይቀልጣል፣ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል።” 2ኛ ጴጥሮስ 3:10 ምናልባት ይህ በዘመናችን ያለውን የኑክሊየር ፍጥጫና ሊፈጠር ያለውን ጥፋት ያመለክት ይሆን? እያሉ የሚጠይቁ የመጽሃፍ ቅዱስ ትንቢት ምሁራን ብዙ ናቸው። በእርግጥ ጌታ አምላክ ሰማይንና ምድርን ለማቃጠል የሰዎች የኑክሊየር የጦር መሳሪያ አያስፈልገውም። ነገር ግን የሰው ልጅም ራሱንና ይችን ዓለም ለማጥፋት አቆብቁቦ ባለበት በዚህ ሰዓት ይህን ማሰቡ ከአድማሱ ውጭ አይደለም።
ሐዋርያው ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት ላይ ሳለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መልአኩን ልኮ ከገለጠለት ብዙ ነገሮች አንዱ የአራቱ ፈረሶች መለቀቅ ነው። የመጀመሪያውን ነጭ ፈረስ ተከትሎ የሚመጣው ሁለተኛው ፈረስ መልኩ ዳማ (ቀይ) ሲሆን በእርሱም ላይ የተቀመጠው ሰላምን ከምድር ላይ እንዲወስድ እና ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ የማድረግ ስልጣንና ታላቅ ሰይፍ የተሰጠው ነው። በዚህ በቀዩ ፈረስ ላይም ሆነ በሌሎቹ በሶስቱ ፈረሶች ላይ የሚቀመጡት ምን ዓይነት ፍጥረታት እንደሆኑ ባይነገረንም፣ የእግዚአብሔርን ቁጣ በምድር ላይ የሚገልጡ፣ ትእዛዝ ሲሰጣቸው የሚሰሙና ያንንም ትዕዛዝ በትክክልና በፍጥነት የሚያስፈጽሙ እንደሆኑ እናነባለን። የሶስተኛው ቀይ ፈረስና በሱ ላይ ያለው ተቀማጭ ተልእኮ እጅግ የሚያስፈራ ነው። ብዙ የስነመለኮት አስተማሪዎች እነዚህ አራት ፈረሶች የሚለቀቁት ክርስቲያኖች ከምድር ላይ ከተነጠቁ በኋላ ነው ብለው ያስተምራሉ። እነዚሁ ምሁራንና አስተማሪዎች፣  ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የተቀበሉ ክርስቲያኖች በምድር ላይ እያሉ በዮሐንስ ራእይ ላይ የተጻፉት ብዙዎቹ ትንቢቶች  (እነዚህን አራቱን ፈረሶችንም ጨምሮ) አይፈጸሙም ይላሉ። የትንቢት አፈጻጸም ቅደም ተከተል ይህ ነው ወይም ነው ብሎ መናገር ብዙ ጥንቃቄና የጌታን ፍርሃት የሚጠይቅ ስለሆነ ይህኛው ወገን ትክክል ነው ያኛው ትክክል አይደለም ማለት አያሻም። ነገር ግን በዓይናችን የምናየውና የምንሰማው ነገር ሁሉ የትንቢትን ፍጻሜ የሚመስል ከሆነ፣ በእርግጥ ትንቢት ሊፈጸም ነው ወይ ወይስ አይደለም ብሎ የእግዚአብሔርን ቃል መመርመር፣ በእውነተኛ ጸሎትና በተሰበረ ልብ የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ አስፈላጊ ነው። ከእስራኤልና ታሪክ እንደምንማረው ተምረናል፣ አውቀነዋል፣ የኛ ዶክትሪን ብቻ ትክክል ነው ያሉት የእስራኤል የሃይማኖት መሪዎች በራሳቸ እውቀትና አስተያየት፣ እንዲሁም በቤተ መቅደስ ሥርዓታቸውና በሥልጣናቸው ላይ ከመመካታቸው የተነሳ እግዚአብሔር ወልድ ራሱ በመካከላቸው ሲመላለስ ሊያዩት አልቻሉም። ከጌታ ደቀመዛሙርት ብዙዎች ጌታ ኢየሱስ ስለኢየሩሳሌም መፍረስና ስለእስራኤል መበተን በተለይ በሉቃስ 21 ቁጥር 20 እስከ 24 የተናገረውን ስላስተዋሉና ስለታዘዙ 70 ዓም በኢየሩሳሌም ከሆነው ፍጅት አምልጠዋል፣ ለእኛም የደረሰውን ወንጌልን በስደት ምድራቸው ሰብከዋል። ሌሎች ግን ያንን የጌታን ማስጠንቀቂያ እምቢ ስላሉ በቤተ መቅደሱና በኢየሩሳሌም ከተማ ላይ በሆነው ጥፋትና ፍጅት ሞተዋል። በዚያ 0070 ዓም በኢየሩሳሌም ስለሆነው ፍጅት የሚያስረዱ ምሳሌዎችን እንዳላካፍላችሁ ቦታ ያጥረኛል። ባለፉት አራት ዓመታት፣ ማለትም 2013 ጀምሮ በምድር ላይ የዓመጽ መንፈስ እንደ ታላቅ ማዕበል ተነ ይህ ዓመጽ ብዙ መልኮች አሉት። አንደኛውና ዋነኛው በእግዚአብሔር ቃል ላይና እግዚአብሔር በደነገገው የተፈጥሮ ሥርዓት እንዲሁም ሞራላዊ ገደቦች ላይ የተነሳ ዓመጽ ነው። ሌላው ደግሞ ሰላማዊ፣ የበለጸጉና ያደጉ ናቸው በሚባሉት አገሮችና ህዝቦችም ዘንድ ሳይቀር ህዝቦች በህዝቦች ላይ እና መንግስታት በመንግስታት ላይ መነሳሳታቸው ነው። ቀዝቃዛው ጦርነት አበቃ፣ ሰላም ሆነ ከተባለባቸው ከ1990ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በምድር ላይ ሰፍኖ የነበረው አለም አቀፋዊ መረጋጋት በድንገት ወደ ቀውስ የገባ ቢመስልም የተዘናጋነው እኛ ነን እንጂ በበምስራቅና በምእራብ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ሰላም የእውነት አልነበረም። ያለንበት ጊዜ እጅግ አደገኛ ነው። ለምድር መሪዎች ሁሉ እንጸልይ። በተለይም ደግሞ የክርስቲያን አገሮች ናቸው ለሚባሉት ለአሜሪካና አጋሮቿ እና ለሩሲያ መሪዎች በተጨማሪም ደግሞ የጦርነት ከበሮን እየደለቁ ላሉት የሌሎቹ መንግስታት መሪዎች ወደልባቸው መለስ ብለው ሰብዓዊነታቸውን እንዲያስቡ፣ በየቢሮዎቻቸውና በየምሽጎቻቸው ሆነው ወደጥፋት የሚገፋፉአቸውን የክፉ መካሪዎች እምቢ እንዲሉና ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ሥልጣን ተላልፈው ሊያጠፉት የማይችሉትን የጦርነት እሳት እንዳይለኩሱ መጸለይ የእኛ ተግባርና ግዴታ ነው። የመንግስታትን ልብ እንደ ቦይ ውሃ መምራት የሚችለው አምላክና የምድር ሁሉ ጌታ እኛው የምናመልከው የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰዎች ሁሉ፣ እነዚህን የምድር ታላላቅ መንግስታት መሪዎችንም ጨምሮ፣ ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ለዘለለም እንዲኖሩና ይህን ምድርንም በአግባቡ እንዲንከባከቡ ነው። የተጻፈው ሁሉ ሊፈጸም የግድ ነው። እኛ ግን ጌታ ራሱ እንዳደረገው ከማማለድ ወደ ኋላ ልንል አይገባም። ጌታ ይባርካችሁ፣ ይጠብቃችሁም። ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ። 96% Russian nuclear ballistic missiles ready to be used at any moment


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...