ዓለም ለትልቅ ጦርነት እየተዘጋጀች ይመስላል፣ ክፍል 2

ዓለም ለከፍተኛ ጦርነት እየተዘጋጀች ይመስላል 
ክፍል 2 (ከክፍል 1 የቀጠለ - ከጽሁፉ መጨረሻ ላይ የሚገኘውን የድረ ገጽ ማገናኛ በመጫን የተያያዘውን ዜና ተመልከቱ)

ይህ ያስቆጣቸው ምእራባውያኑም ሩሲያን G8 ከሚባለው ቡድን ውስጥ በማስወጣትና የተለያዩ የኢኮኖሚ እቀባዎችን በሩሲያ ላይ በመጣል ተበቀሉ። በዩክሬን የተፈጠረው ቀውስ በአገሪቱ በስተምስራቅና በስተደቡብ ምስራቅ ያሉ እና የሩሲያ ዝርያ ያላቸው ህዝቦች የሚበዙባቸው ክልሎችም ተስፋፋ። ከነዚህም ክልሎች ሁለቱ ከልሎች ከማእከላዊው የዩክሬን መንግስት ለመገንጠል እና ወደሩሲያ ለመደባለቅ ያደረጉት እንቅስቃሴ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ተለውጦ ብዙ ሺ ህዝብ አልቆአል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩም ተሰደዋል። ምእራባውያኑም ይህንን ጦርነት የምትደግፈው ሩሲያ ናት በማለት ይከሳሉ። ሩሲያ እነዚህን ለመገንጠል የሚፈልጉ ክልሎች ወደራሷ ግዛት ለማስገባት ፍላጎት እንደሌላት ብትገልጽም፣ በነዚያ ክልሎች ያሉትን ሩሲያዊ ዝርያ ያላቸውን ህዝቦች መደገፍዋን ግን አትደብቅም። ይህ ሁኔታ እየተካረረ መጥቶ ዛሬ አሜሪካና አጋሮቿ ሩሲያ ሌሎችንም የምስራቅ አውሮፓ አገሮችን ልትወርና የአውሮፓን ሰላም ልታናጋ ትችላለች በሚል ሰበብ ብዙ ሰራዊትን እና የጦር መሳሪያዎችን በሩሲያ ድንበር አጠገብ ወዳሉ አገሮች እያሰፈሩ ነው። ባለፉት ስምንት ወራት አሜሪካና አጋሮቿ ከ2500 በላይ ታንኮችን እና ከ100 በላይ የጦር ሄሊኮፕተሮችን እንዲሁም በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ወታደሮችን ወደ ላትቪያ፣ ሊትዌኒያ፣ ኢስቶኒና፣ ፖላንድ እና ሌሎችም አገሮች አስገብተዋል። የሩሲያን ስትራቴጂካዊ የኑክሊየር ሚሳኤሎች ሊያመክን እና የሩሲያንም ግዛት ለምእራባውያን ሚሳኤሎች ሊያጋልጥ የሚችል የራዳር ጣቢያ  አሜሪካ በቡልጋሪያ የከፈተችው ባለፈው ዓመት ነበር። ሩሲያም በበኩሏ የጦር ሰራዊቷን በማስፋፋት፣ እንደገና በማዋቀርና በአዳዲስ የጦር መሳሪያዎች በማስታጠቅ ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ ከጀመረች ውሎ አድሮአል። በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን በአሜሪካና በሶቪየት ህብረት መካከል ተደርገው የነበሩ ስምምነቶች ሁለቱ አገሮች የኑክሊየር መሳሪያዎቻቸውን በከፍተኛ ቁጥር እንዲቀንሱ አስችለዋቸው ነበር። ዛሬ ግን ከነዚያ ስምምነቶች አንዳንዶቹ ስለፈረሱ አዳዲስ የጦር መሳሪያዎችን የመስራቱ እሽቅድምድም ተጧጡፏል። ታዲያ ይህ ሁሉ ወዴት ነው የሚያመራው የሚለውን ለመመለስ እጅግ አዳጋች ባይሆንም፣ በጉዳዩ ላይ የቅርብ እውቀቱ ያላቸውን መስማቱ ደግሞ እረፍት የሚነሳ ጉዳይ ነው። በዓለም ላይ ያለው የሰላም ቀውስ በሩሲያና በምእራባውያን መካከል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብዙ አገሮችንም የሚነካካ ጉዳይ ነው። በደቡብ ኮሪያ የሰፈረው የአሜሪካ ጦርና ጃፓን ያሰጉኛል ብላ ኑክሊየር ቦምቦችን እና ሚሳኤሎችን እየሰራችና እየፈተሸች ያለቸው ሰሜን ኮሪያ፣ የምእራባውያንን እና በሳውዲ አረቢያ የሚመራውን የሱኒ እስላሞች ኃይል ለመቋቋም ወታደራዊ ኃይሏን በከፍተኛ ደረጃ እየገነባች ያለችው ኢራን፣ በደቡብ ቻይና ባህር፣ በጃፓን፣ በኮሪያ ባህረ ገብ መሬት፣ በጃፓን እና በሌሎችም የእስያ ክፍሎች ቻይና በወታደራዊ ኃይል ያለልክ ያለፈ እንዳትስፋፋ ለመግታት አሜሪካ የምታደርገውን ጥረት ለመቋቋም ቻይና ራስዋ በከፍተኛ ፍጥነት እያደረገችው ያለው የጦር መሳሪያ ማምረት፣ የጦር ሰፈሮችን የመስራትና ወታደሮቿን የማሰልጠን ተግባር፣ ሺያ እስልምናን ከምትከተለው ከኢራንና በሷም ከሚደገፉ በየመን ካሉ ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር በየመን ግልጽ ጦርነት ውስጥ የገባችው ሳውዲ አረቢያና ሌሎችም ትልልቅ የጦር ኃይል ያላቸው አገሮችም በከፍተኛ ፍጥነትና ወጭ ለጦርነት እየተዘጋጁ ነው።

ጦርነትና የጦርነት ወሬ የጌታን ዳግም ምጽዓት መቃረብ ከሚያመለከቱት ነገሮች አንዱ መሆኑን በማቴውስ ምዕ 24 እና በሉቃስ 21 ላይ እናነባለን። እነዚህም ከምጥ ጣር መጀመሪያዎች አንዱ እንጂ ብቸኛ አመላካች አይደሉም። በየትኛውም ዘመን ቢሆን ጦርነት አጥፊና አሰቃቂ መሆኑ የታወቀ ነው። በዚህ ዘመን፣ በተለይም ደግሞ በታላላቆቹ የዓለም መንግስታት በአሜሪካ፣ በሩሲያ፣ በቻይና እና በተባባሪዎቻቸው መካከል የሚነሱ ጦርነቶች በሰው ዘር ላይ ሊያመጡት የሚችሉት ጥፋት ግን እጅግ ከባድና ለመገመት አስቸጋሪ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “እነዚያ ቀኖች ባያጥሩስ ሥጋን የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር” ካለ፣ ሊሆን የሚችለውን ጥፋት የሰው ቋንቋ ሊገልጸው አይችልም። ስለዚህ ክርስቲያኖች ሁሉ ለመንግስታት እና በየደረጃው ላሉ መሪዎች ሁሉ መጸለይ ያስፈልገናል። የተጻፈው ሁሉ የሚፈጸም ቢሆንም ይኼ ያለንበትና የወንጌል ጸጋ ለሰዎች ሁሉ እንዲሰበክ እግዚአብሔር የሰጠን ዘመን ከመዘጋቱ በፊት ኃላፊነታችንን ወንጌልን በመስበክ፣ ለእግዚአብሔር ቃል በመታዘዝ በቅድስና እና በፍቅር በመኖርና ለሌሎች የእግዚአብሔርን ፍቅር በማሳየት ልንወጣ ይገባናል። የሰላም አምላክ ልባችንን ለዚህ ያነሳሳ። ከ2500 በላይ የአሜሪካ ታንኮችና፣ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችና መድፎች አውሮፓ ገቡ 
ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...