አዕምሮ ያለው የአውሬውን ቁጥር ይቁጠረው፣ ቁጥሩ የሰው ቁጥር ነውና፣ ቁጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው። የዮሐንስ ራዕይ 13፡18

አዕምሮ ያለው የአውሬውን ቁጥር ይቁጠረው፣ ቁጥሩ የሰው ቁጥር ነውና፣ ቁጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው። የዮሐንስ ራዕይ 13፡18


 እግዚአብሔር ሰውን በአምሳሉ ሲፈጥረው በዚህች ምድር ላይ ዘሩ እንዲበዛና በእርስዋም ያሉትን ፍጥረታትን እንዲከባከብና እንዲያስተዳድር እንዲጠብቅም ነበር። የሰው ልጅ ያንን በረከት ለመውረስና የተሰጠውን ሥልጣን በሚገባ ለመጠቀም ደግሞ እርሱ ራሱ የሁሉም ነገር ምንጭ ከሆነው ከፈጣሪው ጋር እንዲኖረው የታደለበትን ልዩ ፀጋ በማክበር ለአምላኩ መገዛት፣ እርሱን ብቻ ማምለክና ከእርሱም ጋር ህብረት ማድረግ ያስፈልገው ነበር። ያ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ፍጹም ህብረት በኃጢዓት ምክንያት ሲበላሽ ግን የሰው ልጅ በወደቀው ኪሩብ በሉሲፈርና በጭፍሮቹ የተንኮል ወጥመድ ውስጥ ገባ። የሚያስፈልጉትንም ሆነ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ሲል ከፈጣሪ በተሰጠው እውቀትና ጥበብ ብቻ ከመጠቀም ይልቅ፣ ከጨለማው ዓለም ገዥ የሚወረወሩለትን ቅራቅንቦዎች መለቃቀም ጀመረ። ስር ምሶ ቅጠል በጥሶ ሌላውን ለማጥፋት መርዝ ከመቀመም ጀምሮ፣ መናፍስትን በመጥራትና ከአጋንንት ጋር ቃል ኪዳን በመግባት በሌሎች ላይ መተትን እና ሟርትን ማድረግ የሰው ልጅ በራሱ የፈጠራቸው ሳይሆኑ በወደቁት መላእክት አማካይነት ዲያብሎስ የሰው ልጆችን ያስተማራቸው ብዙ ክፋቶች አካል ናቸው። እነዚህ ኋላ ቀርና የድሮ ነገሮች ናቸው ብሎ የሚያስብ ሰው ካለ ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እነዚህ ነገሮች በምድር ሁሉ እንዴት ተንሰራፍተው እንዳሉ በቂ መረጃ የሌለው ወይም እያወቀ መቀበል የማይፈልግ ሰው ብቻ ነው።
የሰው ልጅ ኑሮውን ለማሻሻልና የተሻለ ህብረተሰብን ለመገንባት የተለያዩ ቴክኮኖሎጂዎችን መፍጠሩና በነዚህም በመረዳት የስራን ሸክም ማቃለሉ እና ፍሬያማነትን ማጠናከሩ መልካምን ሁላችንም ልንረባረብበት የሚገባ ነገር ነው። በዚህ በተያያዘው ዜና ላይ እንደምታዩት፣ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ልእቀት ላይ ደርሰናል በሚሉት አገሮች ባሉ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ መሪዎች የሚተነበየውና ትኩረት ተሰጥቶት ብዙ መዋእለ ንዋይ የሚፈስለት የቴክኖሎጂ እድገት አቅጣጫ የሚያተኩረው ግን ዛሬ ብዙ የዓለምን ህዝቦችን ወጥረው የያዙ የምግብና የንጹህ ውሃ እጥረት፣ የህክምና ችግር፣ ሽብርተኝነትና የሰላም መታጣት ወዘተ አይደሉም። በዚህ ዜና ላይ የተገለጸው ሃሳብ ዋና ምንጭና አራማጅ የሆኑት የጉግል ኮርፖሬሽን የቴክኖሎጂ ዳይሬክተር ሬይ ከርዝዋይል የሚባሉት አሜሪካዊ ብዙ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር የሚታወቁ ሰው ናቸው። ባለፉት አሰርት ዓመታት በጻፉአቸው ብዙ መጻህፍቶቻቸውና በየጊዜው በሚያደርጉአቸው ንግግሮች እኒህ ሰው ብዙ ቴክኖሎጂን የሚመለከቱ ትንበያዎችን አድርገው ከነሱም ውስጥ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆኑት እውን ሆነዋል። ነቢይ ሆነው ሳይሆን እየተሰራ ያለውን አዳዲስ ቴክኖሎጂ በአብዛኛው ስለሚያዉቁና እራሳቸውም ደግሞ በሚሰሩት ነገሮች ውስጥ ተሳታፊ ስለሆኑ ነው። በቴክኖሎጂ ልእቀት ከመታመናቸው የተነሳ እኒህ ሰው የሰውን ልጅ ክቡርነት ሰው ሰራሽ ከሆኑ ኮምፒውተሮችና መሰል ቴክኖሎጂዎች በላይ አድርገው ለማየት ተስኖአቸዋል የሚሉ ብዙ ናቸው።
በተያያዘው ዜና ላይ እንደምታነቡት፣ እኒህ ሰው ባለፉት አስር ዓመታትና ከዚያም በፊት በጻፉአቸው መጻህፍቶቻቸው ላይ እንደ ገለጹት፣ በተለያዩ የቴክኖሎጂ መስኮች የተደረጉ እድገቶች እጅግ የላቀ ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው የተነሳ የሰው ልጅ የሰራቸው ኮምፒውተሮችና በኮምፒውተር የሚመሩ ቁሳቁሶች ከሰው ልጅ ችሎታና አቅም በላይ የሚሆኑበት ጊዜ ከ12 ዓመት እንደማያልፍ አመልክተዋል። በኮምፒውተር፣ በሮቦቲክስ፣ በናኖ ቴክኖሎጂ፣ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና በሲንተቲክ ባዮሎጂ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ የቴክኖሎጂ መስኮች የተደረሰበት የእድገት ደረጃ እጅግ ታላቅ ስለሆነና፣ የሰው ልጅ ደግሞ በተፈጥሮ ባለው ችሎታ ብቻ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች በሚገባ ተቆጣጥሮ ስራ ላይ ለማዋል ስለማይችል እሱ ራሱ በቴክኖሎጂ መሻሻል አለበት። ይህ አይቀሬ ነው እንዲያውም ከዛሬ እስከ ዛሬ አስራ ሁለት ዓመት ድረስ (በ2029 እንደ ኤውሮፓውያን አቆጣጠር) የሰው ልጅ ጭንቅላትና እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በመደባለቅ የቴክኖሎጂ አሃዱነትን (SINGULARITY) ይፈጥራሉ ብለዋል። ከኮምፒውተር ወደ ታብሌት፣ ከታብሌት ወደ ስማርት ስልኮች፣ ከስማርት ስልኮች ወደ ስማርት ሰዓቶች በታላቅ ፍጥነት ተሸጋግሮ የመጣው ቴክኖሎጂ ወደ ኪኒንነት ተለውጦ ሰዎች እንደ መድኃኒት የሚውጡአቸው የሆድ ውስጥ ካሜራዎችና ቀዶ ጥገና የሚያደርጉ ሮቦቶች ከተሰሩ ውለው አድረዋል። ይህ ካስገረመን ዛሬ ደግሞ እንደ መድሃኒት በመርፌ ተወግተው ወደ ሰውነት የሚገቡ፣ ከዚያም በሰውነት ሁሉ ተሰራጭተው የተለያዩ ስራዎችን በሰው ሰውነት ውስጥ የሚሰሩ ናኖ ሮቦትስ ከተሰሩና መፈተሽ ከጀመሩም ዓመታት አልፈዋል። እንደ አንድ ማስረጃ የሚከተለውን ማገናኛ በመጠቀም ከ2 ዓመት በፊት በአንድ የእንግሊዝ ጋዜጣ የወጣ መረጃ ተመልከቱ።(http://www.dailymail.co.uk/sciencetech/article-3000904/Nanorobots-trial-begin-humans-Microscopic-DNA-devices-injected-leukaemia-patient-bid-destroy-abnormal-cells.html)
ታዋቂው አሜሪካው ፈልሳፊ ባለፉት ጥቂት ቀናት ያሉት ባጭሩ የሚለው፡ እኛ የሰው ልጆች ሰው ከሰራቸው ቴክኖሎጂዎች ይልቅ ቀርፋፋ፣ ብዙ ነገር የማይገባንና ይህችንም ምድር ያለአግባብ እያበላሸናት ስለሆነ፣ የተሻልን ፍጥረቶች እንድንሆን በመርፌ የሚወጉ፣ እንደ ኪኒን የሚዋጡ፣ ምናልባትም ደግሞ የሚጠጡ፣ የሚበሉና የሚሸተቱ ወይም ደግሞ በጨረር በቀጥታ ወደሰውነታችን ውስጥ የሚገቡ ጥቃቅን ኮምፒውተሮችና ሮቦቶች ይገጠሙልናል። በዚያን ጊዜ ጭንቅላታችንና ሰውነታችን ከቴክኖሎጂው እኩል ስለሚሆንና ራሱ ከኢንተርኔት ጋር ስለሚያያዝ ጆሮአችን ስልክ፣ አይናችን ቴሌቪዥን፣ አፋችን ድምጽ ማጉሊያ፣ ጭንቅላታችን ደግሞ ታላቅ ኮምፒውተር ይሆናል። ሬይ ከርዝዋይል እንደሚሉት ከሆነ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ከሰውነታችን ጋር ሲዋሃዱ ሁላችን እንደ GOOGLE ሊቅ በመሆን ሁሉን ነገር እናውቃለን። በዓለም ሁሉ ካሉ ሰዎችና ቁሶች ጋር በቀጥታ በጭንቅላታችን ብቻ እንገናኛለን። ለመግዛትም ሆነ ለመሸጥ ወይም ለሌሎች ሰዎች ለመናገርና መልእክት ለማስተላለፍ ወይም ለመቀበል የትም መሄድ አያስፈልገንም። ሰውና ማሽን አንድ ይሆናል ከዚያም በኋላ ዓለም ገነት ትሆናለች ነው የኒህ ሰው ትንበያ ባጭሩ። የረሱት ነገር ግን የሰው ልጅ ስጋና ደም ወይም ጭንቅላትና ጡንቻ ብቻ ሳይሆን በልዑል እግዚአብሔር የተፈጠረ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነው። ሰው የሚወደውና የሞተለት አምላክ አለው።
ቴክኖሎጂ እኛ የምንቆጣጠረው መሳሪያ እንጂ በውስጣችን ገብቶ እኛን የሚቆጣጠር ከሆነ ይህ የሰውም የእግዚአብሔርም ስራ ሳይሆን ሰይጣናዊ ነው። በቤታቸው ወይም በቢሮአቸው ተቀምጠው በሚያዩት ቴሌቪዝንና ስልክ ወይም በሚጠቀሙበት ኮምፒውተር ግለሰቦችንna ሆነ መንግስታትን እየሰለሉ አናስቀምጥም ያሉት ኃያላን አገሮች በኢንተርኔት አማካይነት ወደ እያንዳንዱ ሰው ጭንቅላት ውስጥ መግባት ከቻሉማ ምን ያደርጉ ይሆን። አዋቂዎች ነን ያሉ ኑሮ ያልፍልሃል ብለው ውስጡን በቴክኖሎጂ ከተበተቡት በኋላ፣  ተንኮለኞች፣ ሽብርተኞችና ወንጀለኞች HACK በማድረግና ቫይረስ በመልቀቅ ድሃ ድሃውን ወይም እነሱ የሚጠሉትን ሁሉ እንደማይፈጁት ዋስትናው ምንድ ነው። ደግሞስ በቴክኖሎጂ ለመተብተብና የተሻለ ፍጥረት ለመሆን የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚከፍለው ማን ነው። መቼም ሚስተር ከርዝዋይል እና መሰሎቻቸው ለዓለም ህዝብ ሁሉ በነጻ ይህንን ቴክኖሎጂ ለመቸር የሚፈልጉ ወይም የሚችሉ  አይመስለኝም።  ስለዚህ ሃብታሙ በተራቀቁት ቴክኖሎጂዎች ሲታደስ፣ ድሃ ድሃው ደግሞ በተራረፈውና ምናልባትም ደከምና ረከስ ባሉት ቴክኖሎጂዎች ሊታደስ ነው ማለት ነው?  

መጽሐፍ ቅዱስ 666 የሚባል ነገር ይመጣል ይላል ሲባል የሰማን ሁሉ አሁን ልንነቃ ይገባል። ሃሰተኛው ክርስቶስ የምድር ህዝብ ሁሉ እንዲሰግዱለት የሚያደርግበት ቴክኖሎጂ በደጅ ነው። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው። የሰው ልጅ በምድር ሁሉ ላይ ሊመጣ ታላቅ ስህተትና ጥፋት ሊያመልጥ የሚችለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ነው። በቀኝ እጅ ወይም በግንባር ለሰው ሁሉ ይሰጣል ሲባል ያነበብነውና የሰማነው የሚፈጸምበት ጊዜ እንደደረሰ እንመለከታለን። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ ብሎ ወንጌል እንደተናገረ፣ የንስሃ ቀን ዛሬ ነው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ የመዳን ቀን ዛሬ ነው።  ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ። 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...