ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ሁል ጊዜ ትጉ። ሉቃስ 21፡36



በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሶቪየት ህብረትና ሌሎችም ሶሻሊስት የነበሩ የምስራቅ አውሮፓ አገሮች ሲፈራርሱና የምእራባውያኑን የኤኮኖሚና የፖለቲካ ስርዓት መከተል ሲጀምሩ፣ ቀዝቃዛው ጦርነት አበቃ፣ ከእንግዲህ በኋላ የዓለም መንግስታት በተሻለ መንገድ ይተባበራሉ፣ የመሳሪያ እሽቅድምድም አይኖርም ተብሎ ነበር። ከዚህም የተነሳ ሃብታሞቹ አገሮችና መንግስታት ብዙውን ጊዜአቸውን ፣ ገንዘብና ጉልበታቸውን ወደ ልማት ስለሚያውሉት ዓለም በፍጥነት እየሰለጠነች፣ እያደገችና እየበለጸገች ትሄዳለ፣ ምርትና ንግድ የበለጠ ይስፋፋል፣  ችግርና ድህነት ይቀንሳል፣ ለበሽታዎች መድኃኒት ይገኛል፣ ሰዎችና ህዝቦች የበለጠ ስለሚቀራረቡ ና ስለሚተዋወቁ በዓለም ላይ ሰላም እየሰፈነ ይሄዳል፣ አዳጊ አገሮች የበለጠና የተሻለ ድጋፍ ያገኛሉ ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር። ከነዚህ ተስፋዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ለናሙና ያህል እውነት ሆነው ቢገኙም፣ ያ ብዙ ህዝቦችና አገሮች ተስፋ ያደረጉበት የቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም ብዙም ውሎ ሳያድር እጅግ ብዙ ህዝብን በፈጁ ጦርነቶች ተተካ። በቀድሞይቱ ዩኮዝላቪያ፣ በሩዋንዳ፣ በኮንኮ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፣ በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅ፣ በሶሪያ ፣ በሊቢያ፣ በየመን የተለኮሱትና አሁንም እየነደዱ ያሉት ጦርነቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ በዓለም ሁሉ እንደሰደድ እሳት የተስፋፋው ሽብርተኝነት እጅግ ብዙ መንግስታትን እንቅልፍ ከነሳ ውሎ አድሮአል። ይህ እውነታ ደግሞ በብዙ የዓለም አገሮች የሚኖረውን ሰላማዊ ህዝብ የእለት ከእለት ኑሮ በብዙ መንገድ ለውጦታል። በአፍጋኒስታንና  በኢራቅ የተደረጉት ታላላቅ ጦርነቶች የፈጠሩት እልቂት፣ የህዝቦች መፈናቀልና የሰላም መናጋት ገና መፍትሔ ሳያገኝ አዳዲስ ጦርነቶች በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በየመን ከተለኮሱ ዓመታት ተቆጠሩ። ሶቪየት ህብረት ከፈረሰች በኋላ ያለኔ ማን አለ ብላ ያሻችውን ሁሉ በዓለም ዙሪያ ለማድረግ የዘመተችው አሜሪካና፣ ቀስ ብላ በማንሰራራት “የለም እኔም አለሁ ከምትለው ሩሲያ እንዲሁም ቻይና መካከል የተፈጠረው ውጥረት ከፍተኛና ለዓለም ሰላም እጅግ አስጊ እንደሆነ ብዙ ታዛቢሶች ያስጠነቅቃሉ። ለጦርነት የሚደረጉ ዝግጅቶችና የመሳሪያ ቴክኖሎጂ እድገት እሽቅድምድም በሚያስገርም ፍጥነት በየእለቱ እየጨመረ መሆኑ ምንም አከራካሪ አይደለም። በአሜሪካና በሩሲያ፣ በቻይና፣ በኢራን፣ በሶሪያ እንዲሁም በሰሜን ኮሪያ መካከል ያሉት ከፍተኛ ውጥረቶች ብቻ እንኳን ምድራችንን ሊጠፋ ወደማይችል የጦርነት ሞገድ ውስጥ ሊከቷት እንደሚችሉ ብዙዎች እያስጠነቀቁ ነው።
በእንቅርት ላይ  ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ዓለም አቀፋዊና የግብረ ሰናይ ድርጅቶች በተደጋጋሚ ከሚያወጧቸው ማስጠንቀቂያዎች አንዱና ዋነኛው የአደገኛ ህዋሳት (SUPER BUGS) መባዛትና ብዙ ህዝብን ሊፈጁ የሚችሉ የወረርሽኝ በሽታዎች ቁጥር መጨመር ነው። ባለፉት 15 ዓመታት  እንኳን SARS, MERS, EBOLA, Swine Flu, Bird Fl;u, Salmonella, ZIKA Virus ወዘተ የሚባሉ ተውሳኮችና በሽታዎች ብዙ ሺ ህዝቦችን ፈጅተዋል። አሁንና ወደፊት ይከሰታሉ ተብለው የሚነገሩ በሽታዎች ደግሞ ክትባት ወይም መድኃኒት እንኳን ሊገኝላቸው የማይችሉ እንደሚሆኑ ከሚናገሩት መካከል ባለብዙ ሃብቱ የMICROSOFT ባለቤት ቢል ጌትስ ይገኙበታል።  ድርቅና ረሃብ ብዙ አገሮችን እንደገና እየጎበኘ ባለበት በዚህ ዘመን፣ ጎርፍ፣ የመሬት መደርመስ፣ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታና ሌሎችም የተፈጥሮ አደጋዎችም የራሳቸውን ጥፋት እየሰሩ ነው።
የዓለምን ሁኔታ በቅርቡ የሚከታተሉ አዋቂዎችና እንደ ሚካኤል ጎርባቾቭ ያሉ የቀድሞ መሪዎችም ሳይቀር ዓለማችን እጅግ አደገኛ ወደሆነ ሌላ የዓለም ጦርነት እየተቃረበች መሆኑን ሲያስጠነቅቁ ከርመዋል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በአሜሪካ የተደረገው የመንግስት ሽግግር አገሪቱ ከሩሲያ፣ ከቻይና፣ ከኢራን፣ ሰሜን ኮሪያና ሌሎችም አገርች ጋር ያላትን ውጥረት ያረግበው ይሆናል ተብሎ የተገመተውም ቀቢጸ ተስፋ ከመሆን የዳነ አይመስልም። የአውሮፓ ህብረት በእንግሊዝ መውጣት ሲታወክ፣ ሌሎች ብዙ አገሮችም ይከተላሉ የሚለው ስጋት ትልቅ መናጋትን ፈጥሮአል። በእንግሊዝ ተጀምሮ ወደ አሜሪካ የተሻገረውና አሁን ደግሞ በፈረንሳይ፣ በጀርመን፣ በጣሊያንና በሌሎች አገሮችም ይከሰት ይሆናል ተብሎ የሚፈራው የፖለቲካ ለውጥ፣ ከመካከለኛው ምስራቅና መረጋጋት ከሚጎድላቸው ብዙ አገሮች ወደ ምእራቡ ዓለም የሚጎርፈው የስደተኛና የተሻለ ኑሮ ፈላጊ ህዝብ ብዛትም ከፍተኛ ውጥረትን ፈጥሮአል። ባለፈው ሳምንት እንደ ጻፍኩት የቴክኖሎጂ እድገት ከፍተኛ ቦታ ላይ ስለደረሰን፣ የዘመኑ ባለሃብቶች እንዲሁም አዋቂዎች የሰው ልጅ ራሱ ኋላ ቀር ሆኖአልና የኮምፒውተር ቴክኖሎጂን በጭንቅላቱና በአካሉ ውስጥ በማስገባት ሰውን ራሱን እናሻሽለዋለን በማለት ሲያቅዱ የነበረው ሃሳባቸው ከምርምር ማእከሎችና ከምስጢርነት ወጥቶ በመገኛኛ ብዙኃን በግልጽ እየተናፈሰ ይገኛል።

ይህን ሁሉ ስንመለከትና፣ ከጥቂት ዓሰርት ዓመታት በፊት በምድር ላይ ከነበረው ተስፋ ሰጭ የሚመስል ሁኔታ ጋር ስናስተያየው መጽሐፍ ቅዱስ “ሰላምና ደህንነት ነው ሲሉ ምጥ እርጉዝን ሴት በድንገት እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል፣ ከቶም አያመልጡም” ( 1ኛ ተሰሎንቄ 5፡1-4) የሜለው የትንቢት ፍጻሜ ይመስላል። ያለጥርጥር ዓለም በታላቅ ፍጥነት እየከነፈችበት ያለው አካሄድ ከእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ እውነት የራቀና የሰውን ልጅ የወደፊት የሰላም ኑሮ እጅግ የሚያሰጋ ነው። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል አሁንም ቢሆን የመመለስ ተስፋ እንዳለ ይናገራል። እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሰጠው ምህረትና የዘለዓለም ሕይወት ተስፋ በሩ ዛሬም አልተዘጋም። ለእያንዳንዱ ሰው በግሉም ሆነ ለዓለማችን በአጠቃላይ ያለው እውነተኛ ተስፋ መሰረቱ ይህ ብቻ ነው። ክርስቲያን ነኝ የሚል ሁሉ በዚህ እውነት ራሱን በመመዘን የወንገልን የምስራች ለሌሎች ሁሉ የማድረሻው ጊዜ ይህ ነው። የዓለማችን ዋነኛው ችግር ኃጢዓት፣ መፍትሔው ደግሞ ክርስቶስ ነው። የማታ የማታ ፍጥረት ሁሉ ይህን እውነት ያውቃል። ዛሬ ንስሃ በመግባት ለማይመለስ ሰው ሁሉ ግን ያ እውቀት ለፍርድ እንጂ ለመዳን አይሆንም። ስለዚህ ሁላችንም በምድር ላይ ሊመጣ ካለው ጥፋት ለማምለጥ እንድንችል በንስሃ እንመለስ፣ የተመለስንም ሌሎችን እንመልስ። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...