ሐሰተኛው ክርስቶስና የምስጢሯ ባቢሎን
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ፍጻሜ፣ ስለ ዳግም ምጽዓቱ፣ ስለሚመጣው ፍርድና
ስለ እግዚአብሔር መንግስት መገለጥ ለሐዋርያው ዮሐንስ የገለጻቸውን ብዙ ትንቢቶች በዮሐንስ ራዕይ ውስጥ እናነባለን። ባለፉት ሁለት
ሺ ዓመታት ብዙ የቤተ ክርስቲያን ታላላቅ መሪዎች፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ምሁራንን፣ የታሪክ አዋቂዎች እና ታዋቂ ክርስቲያን ሳይንቲስቶችም
ሳይቀሩ እነዚህን ትንቢቶች ከማንኛውም መጽሐፍ በበለጠ ሲመረምሩ፣ ሲተነትኑ እና ለመረዳት ሲሞክሩ ኖረዋል። ከነዚህ ትንቢቶች ውስጥ
የተፈጸሙ ብዙ ቢኖሩም አብዛኛዎቹ ግን ገና የሚፈጸሙ ናቸው። ከጌታ መምጣት አስቀድሞ ከሚሆኑት ዋና ዋና ነገሮች ውስጥ አንዱ የሃሰተኛው
ክርስቶስ መገለጽ ነው። በዮሐንስ ራዕይ ላይ እና በትንቢተ ዳንኤል ሰባት ራሶች እና አስር ቀንዶች ያሉት አውሬ ተብሎ የተጠቀሰው
ሃሰተኛው መሲህ የሚገለጸው ደግሞ ታላቂቱ ባቢሎን እና የምስጢር ባቢሎን ተብላ ከምትጠራ ሴት ጋር ተያይዞ እንደሆነ በዮሐንስ ራዕይ
ምእራፍ 17 እና 18 ላይ እንመለከታለን። በነዚህ ምእራፎች ላይ የተጠቀሰችውን ታላቂቱ ጋለሞታ ማንነት በመተንተን ባለፉት ብዙ
መቶ ዓመታት የተጻፉና የትንቢት ትንተናዎች እንደሚያመለክቱት ታዲያ “የምስጢር ባቢሎን” ወይም “ጋለሞታ” የምትባለው በመጨረሻው
ዘመን በምድር ላይ ተንሰራፍታና በአደባባይ ክርስትና መሰል ሀይማኖትንና ምድራዊ ፖለቲካን በመደባለቅ ሰማያዊውንና ምድራዊውን ነገር
ሁሉ ከአውሬው ጋር በመተባበር ልትገዛ የምትነሳ ዓለም አቀፍ “የሃይማኖት” ድርጅት እንደምትሆን ሲያመለክቱ ከርመዋል። ከነዚህም
ብዙዎቹ የዚህች ጋለሞታ ድርጅት ዋነኛው ማእከል በሮም የሚገኘው የካቶሊክ ቤ/ክ ዋና መስሪያ ቤትና ከሱም ጋር የተያያዙ ሌሎች ድርጅቶች
ሊሆኑ እንደሚችሉ እጅግ ብዙ ጸሃፊዎች በቅርቡም ሆነ ከረጅም ዘመናት በፊት በሰፊው ጽፈውበታል። የነዚህ ጸሃፊዎች ግምት ከእውነቱ
ብዙም የራቀ እንዳልሆነ ደግሞ ከራስዋ ከቫቲካን የወጡ እንደ FATHER ማላኪ ማርቲን ያሉ የካቶሊክ ምሁራንና ከፍተኛ የሃይማኖት
መሪዎች በሰፊው የጻፉበት ጉዳይ ነው። ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት እንኳን ከተለያዩ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ መዋቅር
ጋር የጠበቀ የውስጥ ግንኙነት ያላቸው እንደ ሊዮ ሊዮን ዛጋሚ ያሉ ጸሃፊዎች የሮሟ ቫቲካን ሰዎች እንደሚገምቱት በቅንነት እግዚአብሔርን
የሚያመልኩ የብዙ ካቶሊክ ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ራስ ከመሆንዋ ይልቅ በብዙ ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካና ከዚያም ጠንከር ያሉ ጉዳዮች
ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያላት ድርጅት እንደሆነች አስረድተዋል። እዚህ ጋ መገንዘብ ያለብን አንድ እውነት አለ። ብዙዎቹ የካቶሊክ ቤተ
ክርስቲያን ምእመናን ይህንን በሮም ያለችው ዋና ድርጅታቸው አለችበት የሚባለውን ነገር ሁሉ ያውቃሉ ወይም በዚያ ይስማማሉ ማለት
አይደለም። ይህ ነገር የሚከነክናቸው አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምሁራንና መሪዎች ደግሞ በግልጽም ሆነ በስውር የቫቲካንን አሰራር
በመቃወምና በማጋለጥ ምእመናኖቻቸውን እያስተማሩ ይገኛሉ። በቅርብ ጊዜ እንኳን በአሜሪካ የሚገኙ እንደዚህ ያሉ ካቶሊኮች፣ አሁን
ቫቲካንን የሚመሩት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ የበፊቱንና በህይወት እስካሁን ያሉትን ቤኔዲክት 16ኛውን በመጋፋት አሁን ከስልጣን በወረደው
በአሜሪካው መንግስት ድጋፍ ጳጳስነቱን ይዘዋል የሚለው ጥርጣሬና የአሜሪካም መንግስት በዚህ ጉዳይ እጁን አስገብቶ ከሆነ እንዲጣራ
አዲሱን የአሜሪካ መንግስት ፕረደንት በደብዳቤ ጠይቀዋል።
በዚህ ዜና ላይ እንደምናየው ደግሞ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ 27ቱ የአውሮፓ ህብረት መሪዎች እንዴት አድርገው ህብረታቸውን
መጠበቅ እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከመንግስት በላይ መንግስት የሆነው የአውሮፓው ህብረት አያስፈልገንም የሚሉ በየአገሩ ያሉ የፖለቲካ
ፓርቲዎችንም በማውገዝ፣ የሚከተሉት “ለአገሮቻችን ህዝቦች ብቻ እናስባለን” የሚለውን መመሪያቸውን አደገኛ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አንድ ጊዜ ክርስቲያን የሆኑትንም ሆነ ያልሆኑትን ስደተኞች እግር በማጠብ የክርስቶስን ምሳሌ የተከተሉ ሆነው ለመቅረብ የሚሞክሩት
እኒህ ሊቀ ጳጳስ ሌላ ጊዜ ደግሞ አገሮች የትኛውን የፖለቲካ መስመር መከተል እንዳለባቸው ዲስኩር ያደርጋሉ። ባለፈው ዓመት የአሚሪካ
ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በሚካሄድበት ጊዜ በሜክሲኮ በመገኘት፣ በአገሮች መካከል አጥር ለማጠር የሚፈልግ መሪ ክርስቲያን አይደለም ብለው
በመናገር ዛሬ በአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ከተቀመጡት ዶናልድ ትረምፕ ጋር እሰጥ አገባ ገብተው እንደሆነ አይዘነጋም። እንዲሁም ደግሞ
በእስራኤልና በፍልስጥኤማውያን መካከል ላለው ስር የሰደደ ጠብ መፍትሔ አመጣለሁ ብለው እስራኤልንና ፍልስጥኤማውያን የሚኖሩባቸውን
የምእራብ ዮርዳኖስ ክልልና የቀረውን የእስራኤልን ግዛት ጎብኝተዋል፣ የሁለቱን ወገን መሪዎችም ቫቲካን ድረስ ጋብዘው ጸሎት አደረግን
ብለዋል። በእውነትም በቫቲካን ባደረጉት ስብሰባ እሳቸው የክርስቲያን ተወካይ፣ የእስራኤሉ ፕሬዝደንት የአይሁድን እምነት ወክለውና
የፍልስጥኤሙ አስተዳደር ፕሬዝደንት ደግሞ በአብዛኛው እስላም የሆነውን ህዝባቸውን ወክለው ለሰላም ጸልየው ከሆነ ጳጳሱ ትልቅ ስራን
ሰርተዋል ማለት ነው። ብዙዎች ግን ጸሎቱ የመሸፈኛ ነው እንጂ ያካሄዱት የፖለቲካ ስብሰባ ነው ሲሉ ተችተዋል። ብዙ ታዛቢዎች የሃይማኖት
አባቶች የተጣሉን ማስታረቃቸውና ህዝብን ለሰላም ማስተባበራቸው እጅግ መልካምና ተገቢ ተግባር መሆኑን እና ይህም ደግሞ በቫቲካን
አለመጀመሩን ያመለክታሉ። ብዙ ጸሃፊዎችንና የትንቢት ምሁራንን የሚከነክነው ግን ይህች ቤተ ክርስቲያን ነኝ ብላ የምትጠራው ቫቲካን
ለምን በአለም አቀፍ ደረጃና በየአገራቱም ፖለቲካ ውስጥ በመግባት ይህኛው ጥሩ ነው፣ ያኛው መሆን የለበትም በማለት የፖለቲካ ወገንተኝነት
ውስጥ መዘፈቋን ነው። ከዚህም በላይ ብዙዎችን የሚያስገርመው ደግሞ መንግስትና ሃይማኖት ለየብቻው እንደሆነ እናምናለን የሚሉት የሰለጠኑት
የአውሮፓ መንግስታት (እና ሌሎችም) ቫቲካን አለቃቸው እንደሆነች ያህል በመቀበል እኒህ ጳጳስና ከእርሳቸውም በፊት እንደ ዮሐንስ
ጳውሎስ ሁለተኛው ያሉ ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት የሚናገሩአቸውን ነገሮችና
የፖሊሲ መመሪያዎች የሚቀበሉ መምሰላቸው ነው። በመሰረቱ የቤተ ክርስቲያንን ስራ የክርስቶስን ወንጌል መስበክ፣ ምእመናንን ለእግዚአብሔር
መንግስት ማዘጋጀትና በዚህ ምድር ህይወታቸው ደግሞ ለየአገሮቻቸው
መልካም ዜጎች እንዲሆኑ መርዳት ነው። ምእመናን በየግላቸው የራሳቸው የፖለቲካ፣ የፍልስፍናና ሌሎችም አስተያየቶች ሊኖሩአቸው ቢችሉም፣
አንዲት ቤተ ክርስቲያን ነኝ የምትል ድርጅት ግን ከራሷ ምእመናንም አልፋ የብዙ አገሮች መሪዎችንና ህዝቦችን ይህ የፖለቲካ መንገድ
ልክ ነው፣ ያኛው አደገኛ ነው በማለት ያለቦታዋ ስትዳክር መገኘቷ መንፈሳዊ አላማዋን የሳተች ያደርጋታል የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ለዚህም
ይመስላል ብዙ የትንቢት ምሁራንና የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች ቫቲካን የምድር ጋለሞታዎች ሁሉ እናት፣ የምስጢር ባቢሎን የተባለችው
ሴት ሳትሆን አትቀርም ወደሚል ድምዳሜ የደረሱት። የማይገለት የተከደነ፣ የማይታወቅም የተሰወረ የለምና ዛሬ ምስጢር የሚመስለው ሁሉ
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ሲመጣ ግልጽ ይሆናል። ባለፉት አስር በሚበልጡ ዓመታት ብዙ የዚህች ቤተ ክርስቲያን (ወይም ድርጅት)
ቄሶችና የተለያዩ ባለስልጣናት በሰዶማዊነት፣ ህጻናትን በመድፈርና በሌሎችም አሳፋሪ ጉዳዮች ሲታሙና ሲወቀሱ መኖራቸው በዜና አውታራት
ሁሉ ሲዘገብ የነበረ ነው። ታዲያ የገዛ ቤታቸውን እንኳን ገና በሚገባ ያላጸዱት እኒህ የቫቲካን መሪ መንፈሳዊና ሞራላዊ ስልጣኑን
ከየት አግኝተው ይሆን የ27ቱን የአውሮፓ መሪዎች በዚህ ሂዱ፣ በዚያ አትሂዱ ለማለት የቃጡት? ባለፉት መልእክቶቼ እንዳልኩት ሁሉ፣
እንደዚህ ባለ ጊዜ የእውነተኛ ክርስቲያን ድርሻና ሃላፊነት እኒህ መሪና ሌሎችም የእምነትም ሆኑ የፖለቲካ መሪዎች የእውነትና የጥበብ
ሁሉ ምሰሶ የሆነውን እግዚአብሔርን በመፍራትና ንስሃ በመግባት በክርስቶስ በእውነት እንዲያምኑና ዓለሙን ሁሉ ከሚያስተው ከዲያብሎስ
መንፈስ እንዲጠበቁ መጸለይ ነው። እድሉን ስናገኝም እውነተኛውን የክርስቶስን ወንጌል ከመመስከር ወደኋላ ማለት የለብንም። ይህን
ልናደርግ የሚያስችለንን ጸጋና የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እግዚአብሔር ያብዛልን። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ