https://www.rt.com/news/379757-your-whole-life-is-hacked/
ሃሰተኛው ክርስቶስ ምድርን ሁሉ ወደሚገዛበት ቴክኖሎጂ ደርሰን ይሆን?
ከላይ ማገናኛው የተሰጠውን ዜና በመጀመሪያ አንብቡት።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ተገልጾ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግስት በምድር ላይ የሚመሰርትበት ጊዜ እጅግ እየተቃረበ መምጣቱን ለማስተዋል፣ በቅዱሳን ነቢያት፣ በሐዋርያትና በጌታም በራሱ የተነገሩትን ትንቢቶች ማጥናት ብቻ ሳይሆን፣ በምድር ላይ በተግባር እየተከናወኑ ያሉትንን ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ መነጽር ቀረብ ብሎ መከታተል ያስፈልጋል። ባለፉት አምስት ዓመታት ብዙ ነገሮች ወደ ፍጻሜያቸው እየቸኮሉ መሆናቸውን ብዙ የትንቢት ምሁራንና መንፈሳዊውን ዓለም በቅርብ የሚከታተሉ ተመራራሚዎች ያስረዳሉ።
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመገለጹ በፊት ግን እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ እንደገና በኢየሩሳሌም በሚሰራው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚቀመጥ የዐመጽ ሰው፣ የጥፋት ልጅ በተለምዶም ሐሰተኛው ክርስቶስ የሚባለው እንደሚገለጽ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ታዲያ ይህ የምድር መንግስታትና ህዝቦች በሙሉ የሚሰግዱለት ዓመጸኛ ወይም ሐሳዊው መሲህ፣ በሚገለጽበት ጊዜ እንዴት አድርጎ ነው የምድር ህዝቦች ሁሉ እንዲሰግዱለት የሚያደርገው የሚለውን ጥያቄ በማንሳት፣ ኮምፒውተር የሚባለው ቴክኖሎጂ እስከተደረሰበት እስከ 20ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ቀልድ ነው እያሉ ያንኳስሱት ነበር። ዛሬ ግን ሰዎች አመኑም አላመኑም ያለጥርጥር እዚያ ዘመን ላይ ደርሰናል። በእጆቻችን የምንይዛቸው፣ የምንኮራባቸውና በመራቀቃቸው የምንወዳደርባቸው ስልኮች (smart phones) ፣ ታብሌቶች፣ በእጅ ላይ የሚታሰሩ (smart watches)፣ እንዲሁም በመኪናዎች፣ በቴሌቪዥን እና የሙዚቃ ማጫወቻዎች፣ በትራፊክ መብራቶች፣ በካሜራዎችና በሌሎችም ብዙ የእለት ከእለት መጠቀሚያ ቁሳቁሶች ውስጥ ያለው ቴክኖሎጂ ሁሉ ያገለግለናል ብለው የገዙትን ሰዎች ወይም ማህበረሰብ ከማገልገል ባለፈ፣ የማንፈልጋቸውንና ሊጎዱን የሚችሉ ነገሮችን እንደሚሰሩ ከተጠረጠረ ውሎ አድሮአል። ይህ ያያዝኩት ዜና በግልጽ እንደሚያስረዳው፣ እነዚህ በገዛ ገንዘባችን የምንዛቸው ቴክኖሎጂዎች፣ ከዓለም አቀፉ መረብ (ኢንተርኔት) ጋር መያያዛቸው ደግሞ በዚህ ዜና ላይ እንደተገለጸው ያሉ ድርጅቶች ሰው በማያስበው መንገድ በየእለቱ የሚወጣ የሚገባበትን፣ የሚሰራውን፣ የሚገዛ የሚሸጠውን፣ የሚያወራውንና ውሎ የሚያድርበትን ሳይቀር በመቃኘት ሪፖርት ስለሚያደርጉ፣ የየእለት ኑሮአችንን እንኳን በነጻነትና በግል ለማካሄድ የማይቻልበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
መንግስታት የአገርን ጸጥታና ሰላም እንዲሁም ህግን ለማስከበር የተለያዩ የመረጃ መሰብሰቢያ መንገዶችን መጠቀም ህጋዊ ስልጣን እንዳላቸው የታወቀ ነው። ነገር ግን በዓለም ላይ ካሉት መንግስታት አንዱ ብቻ የሆነው የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ለምን ይሆን እያንዳንዱን የምድር ሰው ለመሰለል የሚያስችለውን ቴክኖሎጂዎች ፈጥሮና የተፈጠሩትንም ቴክኖሎጂዎች በመጣስ የግለሰቦችን፣ የቤተሰቦችን እና የሌሎች መንግስታትንም ድንበር የሚዘል መረጃ መሰብሰብ ያስፈለገው? ወንጀልን እና ሽብርን ለመግታት ብዙዎቹ ሰላማዊ አገሮችና መንግስታት ከሌሎች መንግስታት ጋር መረጃ በመለዋወጥ ይተባበራሉ። ያም ባይሆን ደግሞ አሜሪካን የሚያህል ታላቅ አገርና መንግስት መረጃዎችን የሚያገኝበት እጅግ ብዙ መንገዶች እያሉ፣ ለምን ይሆን እያንዳንዱን የእጅ ስልክ፣ የቤት ኢንተርኔት፣ ድረ ገጽ፣ የመኪና አቅጣጫ መፈለጊያ መሳሪያ እና ሌሎችንም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ቁሳቁሶችን መድፈር ያስፈለጋቸው? እነዚህ ድርጅቶች፣ የነሱን ስራ የሚደግፉትና የሚተባበሩአቸው ሁሉ አውቀውትም ሆነው ሳያውቁት፣ ፈልገውም ሆነ ሳይፈልጉት መጽሐፍ ቅዱስ ከክርስቶስ ዳግም ምጽዓት በፊት ተገልጾ የምድር ሕዝብ ሁሉ በግድ እንዲሰግዱለት ያደርጋል ለተባለው ሐሳዊው መሲህ ዓለምን እንዲቆጣጠር የሚያስችለውን መረብ እየዘረጉለት ነው እያሉ የሚያስጠነቅቁ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች እና ታዛቢዎች ብዙ ናቸው። ዛሬ የተደረሰበት ቴክኖሎጂና እየተመረቱ ያሉት የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች የተያያዙበት የመረብ አሰራር በእርግጥም በዮሐንስ ራዕይ ምእራፍ 13 ላይ የተጠቀሰው አውሬ አንሰግድልህም የሚሉትን ህዝቦች በሙሉ መግዛትና መሸጥ እንዳይችሉ ለማድረግ የሚያስችሉት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ብዙ የባለጸጎቹ አገሮች መንግስታት ዛሬ ጥሬ ገንዘብን ከገበያ ላይ ቀስ በቀስ እያስወገዱ ዜጎች ለመግዛትና ለመሸጥ ቢወዱም ባይወዱም ኤሌክትሮኒክ ካርዶችን፣ ኮምፒውተሮችን፣ የእጅ ስልኮችን እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ደረጃ በደረጃ እያስገደዱ ነው። smart cards የሚባሉት በኑሮ ዘርፎች ሁሉ እንደ አሸን በፈሉባቸው ሰለጠኑ በሚባሉት አገሮች ሰው መኪና ለመንዳት፣ ምግብና ሌሎች ሸቀጦችን ለመግዛት፣ ገንዘብ ባንክ ለማስገባትም ሆነ ለማውጣት፣ ህክምና ለማግኘት፣ በአውሮፕላንና በሌሎችም መጓጓዣዎች ለመጠቀም ሳይወድ በግድ የግል መረጃዎቹን የያዙ ኤሌክትሮኒክ ካርዶችን ወይም የእጅ ስልኮችን መጠቀም የግድ ነው።
ቴክኖሎጂ በመሰረቱ መልካም ነው። ችግሩ ግን የሰው ልጅ ቴክኖሎጂን ሁሉ ለመልካም አይጠቀምበትም። ከክፉ ሰዎችም ሁሉ በስተጀርባ እስከ ዛሬ በስውር ሲሰራ የነበረው የሃሰተኛው ክርስቶስ መንፈስ ነው። ያ ክፉ መንፈስ ደግሞ እኔ ክርስቶስ ነኝ ብሎ የሚገለጽበት ዘመን እጅግ የቀረበ ይመስላል። የብዙ ሰዎች ልብ ከእግዚአብሔር ፍቅር ይልቅ ቴክኖሎጂን እና ዓለምን እየወደደ በመጣበት በዚህ ዘመን ለሃሰተኛው ክርስቶስ መገለፅ አስፈላጊ የሆኑት ቴክኖሎጂዎችም የተዘጋጁ ይመስላል። ራዕይ 13 እንዲህ ይላል፤ “ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፣ ለዘንዶውም ሰገዱለት፣ ለአውሬስ ስልጣንን ሰጥቶታልና ለአውሬውም፤ አውሬውን ማን ይመስለዋል፣ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት። >>> የአውሬው ስም ወይም የስሙ ቁጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ። አእምሮ ያለው የአውሬውን ቁጥር ይቁጠረው፤ቁጥሩ የሰው ቁጥር ነውና ቁጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።” ራዕይ 13 ከ 4 እስከ 18። ጌታም እንዲህ አለ፣ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ። ማቴ 24፤4 በጌታ መገለጥ ቀን እንዳናፍር ነቅተን ልብሳችንን እንጠብቅ። ጌታ ይባርካችሁና ይጠብቃችሁ።
ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ።
የመለከት ድምጽ ብሎግ የአማርኛን ቋንቋ በተቀዳሚነት ለሚጠቀሙ ሰዎች በሙሉ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የወንጌል የምስራች ለማድረስ፣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመኑ ክርስቲያኖች ደግሞ መሰረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማስተማር ያገለግላል።
ደንበኛ ይሁኑ ለ፡
አስተያየቶች ለጥፍ (Atom)
ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ
በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...
-
የኖኀ ዘመን ፥ ኔፊሊም እነማን ናቸው? ከየት መጡ? ምን አደረጉ? ፍጻሜያቸውስ? ትምሕርት 5 ዘፍጥረት ምዕራፍ 6 “በዚያን ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች ...
-
የኖህ ዘመን እንደነበር የጌታ መምጣትም እንዲሁ ይሆናል፡ ኔፊሊም ከየት መጡ? ከሰው ሴቶች ልጆች የወለዷቸው እነዚያ “የእግዚአብሔር ልጆች” የተባሉት እነማን ናቸው? ትምሕርት 6 ባለፉት 5 ትምህርቶች ጌታ ኢየሱስ...
-
በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም መወለድ ማለት ምን ማለት ነው? ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ፣ May 6, 2018 አንድ ሰው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ዳግም ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊ...
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ