አንድ የዓለም መንግስት ይመስረት የሚለው ሃሳብ እየጨመረ ያለው ለምን ይሆን? ታዋቂው ፕሮፌሰር ስቲቨን ሆውኪንግም ይህ ያስፈልጋል አሉ

http://www.thetimes.co.uk/article/hawking-on-humanity-and-corbyn-jk88zx0w2?#_=_

አንድ የዓለም መንግስት ይመስረት የሚለው ሃሳብ እየጨመረ ያለው ለምን ይሆን?

ባደረባቸው ከፍተኛ የነርቭ ህመም ምክንያት የወንበር ቁራኛ የሆኑት ፕሮፌሰር ስቲቨን ሆውኪንግ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉት ታላላቅ የTheoretical Physics ምሁራንና ተመራማሪዎች በቅድሚያ የሚጠቀሱ ናቸው። ኢሎን መስክ የሚባሉት የደቡብ አፍሪካ ዝርያ ያላቸው አሜሪካዊ ቢሊዮነርና SPACE-X የሚባሉትን ወደህዋ የሚመጥቁ ሮኬቶችን የሚሰራው ድርጅት እና TESLA በሚባለው ስም የሚታወቁትን የተራቀቁ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ሰሪ ድርጅት ባለቤት ደግሞ እንዲሁ በቴክኖሎጂው መስክ ትልቅ ዝናን ያተረፉ ሰው ናቸውው። ታዲያ በዚህ በተያያዘው ዜና ላይ እንደምታነቡት እነዚህ ሁለት ታላላቅ ሰዎች የሰው ልጅ ራሱ የሰራው እና በከፍተኛ ፍጥነት በዓለም ላይ እየተሰራጨ ያለውና ARTIFICIAL INTELLIGENCE በመባል የሚታወቀው ቴክኖሎጂ የሰውን ዘርና ሌላውንም ፍጥረት ደህንነት ስለሚያሰጋ መንግስታት በመተባበር ይህ ቴክኖሎጂ ከቁጥጥር ስር እንዳይወጣ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ሲያሳስቡ ከርመዋል። በዚህ ዜና ላይ እንደምናየው ትንሽ የሚያስገርመው ግን፣ ፕሮፌሰር ሆውኪንግ አሁን ያሉት የዓለም መንግስታት መተባበር ብቻ በቂ መሆኑ ስላሳሰባቸው አንድ የዓለም መንግስት መቋቋም ያስፈልገዋል ማለታቸው ነው። ያ አንድ የዓለም መንግስት ደግሞ አምባ ገነን ሊሆን እንደሚችል ግር የማይላቸው ፕሮፌሰር፣ ያ ሊሆን ቢችልም የሰው ልጅ ያንንም ችግር ቢሆን መወጣት ስለሚችል እንደሳቸው ሃሳብ አንድ የዓለም መንግስት መቋቋሙ የግድ አስፈላጊ ነው። ታሪክን ጠጋ ብለን ከመረመርን አንድ የዓለም መንግስት ይቋቋምልን የሚለው ሃሳብ በኒህ ፕሮፌሰር የተጀመረ ወይም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የመጣ አዲስ ሃሳብ ሳይሆን፣ የሰው ዘር ገና በፈረስ በሚጎተት ጋሪ ይሄድ በነበረበት ዘመንም የነበረ ነው። ለነገሩም እግዚአብሔር ምድርን ሲፈጥር ምድር ሁሉ በአንድ ቋንቋ ነበረች። የአንድነቷም መሰረት እግዚአብሔር በሰው ልጅ መካከል መመላለሱ ነበር። ሉሲፈር ወይም ዲያብሎስ በሚባለው የወደቀ ኪሩብ ማታለል ምክንያት የሰው ልጅ ከአምላኩ ጋር ያለው ግንኙነት ሲበላሽ ግን ሰው እግዚአብሔርን በመግፋት የራሱን መንግስት ለማቋቋም ሲከጅል ሳይወድ በግዱ በዲያብሎስና በሱ ስር በሚተዳደሩ የወደቁ የሰማይ ፍጥረታት ስር መገዛት የግድ ሆነ። ይህ የሆነው ደግሞ በባቢሎን እንደነበር ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 11 ሲያስረዳን፣ ኦሪት ዘዳግም ምእራፍ 32 ቁጥር 7 እስከ 9፣ መጽሐፈ ኢዮብ ምእራፍ 1 እና 2 እንዲሁም ደግሞ መዝሙረ ዳዊት 96፤5 እና ምእራፍ 82 ደግሞ ምድር ዛሬ ወዳለችበት አሳዛኝ ደረጃ እንደደረሰች ዋና ዋና ሃሳቦችን ይሰጡናል።
ይህ የኃጢዓት፣ የጥላቻ፣ የራስ ወዳድነትና የዓመጽ ዘመን ሲያበቃ ጌታ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ በሰላምና በደስታ የሚኖሩበት ምድርና ሰማይም ሁሉ በስሩ የሚተዳደሩበት የእግዚአብሔር መንግስት እንደሚመሰረት ከብዙ ሺ ዘመናት በፊት በተጻፈው በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጾአል። የዚያ መንግስት ንጉስ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከዚያ ከእግዚአብሔር መንግስት መገለጥ ትንሽ ቀደም ብሎ ግን ምድር ሁሉ የሚሰግድለት አንድ ታላቅና ኃይለኛ መሪ እንደሚነሳ፣ የዓለምን ህዝብና መንግስታት ሁሉ በሚያስገርም መንገድና ሰይጣናዊ ጥበብ በማታለልና በመሸንገል፣ እምቢ ያሉትንም በመፍጀት አንድ የዓለም መንግስትን ለአጭር ጊዜ እንደሚመሰርት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ያን መሪ መጽሐፍ ቅዱስ ሃሰተኛው ክርስቶስ፣ የዓመጽ ሰው፣ የጥፋት ልጅ፣ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ፣ ሰባት ቀንዶችና አስራ ራሶች ያሉት አውሬ ወዘተ በማለት ይጠራዋል። ይህን በተመለከተ ግልጽ ትምህርቶችን ከሚሰጡት ክፍሎች ውስጥ ትንቢተ ዳንኤል ምዕራፍ 2፣ ምዕራፍ 7፣ ምዕራፍ 9 እና 11 ፣ የማቴዎስ ወንጌል ምእራፍ 24፣ የሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 21 እና የማርቆስ ወንጌል ምእራፍ 13 እና የዮሐንስ ራዕይ ምእራፍ 13፣ እና 17 አንዳንዶቹ ናቸው። ያ ዓመጸኛ መሪም በስልጣኑ ሲደላደል እኔ እግዚአብሔር ነኝና ስገዱልኝ ከማለት አልፎ የማይሰግዱለትን ሁሉ እንደሚያስገድልም መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አስቀምታል።
በመጨረሻው ዘመን የሚመጣው በሃሰተኛው ክርስቶስ መንፈስ በመመራት በየዘመናቱ ብዙ ኃያላን ነን ያሉ በጦር ኃይል፣ በማባበል፣ በፍልስፍና እና በኃይማኖት አንዳንዴም ከነዚህ ሁለቱን ወይም ሶስቱን ወይም ሁሉንም በማጣመር ዓለምን በሙሉ በስራቸው አድርገው እንደ አንድ መንግስት ሊገዙ እንደተነሱ የቅርብና የሩቅ ታሪክ በዝርዝር የዘገበው ጉዳይ ነው። የባቢሎኑ ናቡከደነጾር፣ የግሪኩ እስክንድር፣ የፈረንሳዩ ናፖሊዮን፣ የእንግሊዝ ነገስታት፣ እና የጀርመኑ ሂትለር ዋና ዋናዎቹ ምሳሌዎች ናቸው። ፕሮፌሰር ሆውኪንግ የተመኙት አንድ የዓለም መንግስት መምጣቱ የግድ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ተናግሮአልና። ነገር ግን ያ መንግስት ዓለም እስከ ዛሬ ድረስ ያላወቀችው አታላይ፣ ፈጽሞ ኢሰብዓዊ እንደሚሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። እስካሁን ድረስ በምድር ላይ የነበሩ ክፉ መንግስታት ፈጽሞ የማይወዳደሩት እብሪትና ጭካኔ የተሞላው መንግስት እንደሚሆንና በሱም ዘመን ብዙ የምድር ህዝብ እንደሚያልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል። ወደ ስልጣን የሚወጣው ግን የምድርን ችግር ሁሉ እንደሚፈታና ምድርን ገነት እንደሚያደርጋት በቴክኖሎጂና በገንዘብ እንዲሁም በሰይጣናዊ ተአምራት በመደገፍ የዓለምን መንግስታትና ህዝቦች በማታለል ነው። ታዲያ ፕሮፌሰር ሆውኪንግ ያ መንግስት አምባ ገነን ሊሆን ይችላል ብለው ሲናገሩ ምን እየተመኙልን እንደሆነ ያውቁ ይሆን? ወይስ እሳቸው የምድርን ህዝብ ወይም የራሳቸው አገር የእንግሊዝን እንኳን በመወከል ይህን ሃሳብ እንዲሰነዝሩ የአገራቸው ህዝብ ድምጽ ሰጥቷቸው ይሆን።

ወገኖች፣ መጽሐፍ ቅዱስ እኛን ክርስቲያኖችን ለአገር መሪዎችና ለባለስልጣናት እንድንጸልይ የሚያስተምረን ዋነኛው ምክንያት እነዚያ መሪዎች ራሳቸው ከክፉ ነገር እንዲጠበቁ፣ እንዲሁም ደግሞ እነሱም እንደኛው ሰብዓዊ ፍጡር ናቸውና በግልም ሆነ በጋራ ከአቅማቸው በላይ ሆኖ የሚመጣ ክፉና አጥፊ መንፈሳዊ፣ ስነልቡናዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎችም ምድራዊ ግፊቶችን በመቋቋም፣ የሚመሩትን እና የሚያገለግሉትን ህዝብ እንደሰብዓዊ ፍጡር በርህራኄ ማስተዳደር እንዲችሉ ነው። የቅዱሳን ጸሎች ታላቅ ነገርን እንደምታደርግ መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ያስተምረናል። ባለፈው መልእክቶቼ እንደ ጻፍሁት፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ባለፉት አምስት ዓመታት የዓመጽ መንፈስ በምድር ሁል ላይ እያንዣበበ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የተጻፈው ሁሉ ሊፈጸም የግድ ነው። እኛ ግን የመጸለይና እድሉን ስናገኝም ለሰዎች ሁሉ፣ ለመሪዎችም ጭምር፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን እውነት፣ እግዚአብሔር ለሰው ዘር ያለውንና ራሱን በመስቀል ላይ በመስጠት የገለጸውን ፍቅሩን እንዲሁም ደግሞ የወንጌሉን ግብዣ ለሚቀበሉ የሰው ልጆች ሁሉ ያለውን አስደናቂ እቅድና ዘለዓለማዊ ተስፋ የመናገር ግዴታ አለብን። የሰውን ልጅ ከሚመጣው ጥፋት ሁሉ የሚያድነው ፕሮፌሰር ሆውኪንግ እና ሌሎቹ የሚመኙት ሰው የሚመሰርተው አንድ የዓለም መንግስት ሳይሆን፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ምኞታቸው ለመልካም ቢሆንም የሚመኙት ነገር ምን እንደ ሆነ ግን በትክክል የተገነዘቡ አይመስልም። ስለዚህ ጸሎታችን ለእርሳቸውና ለመሰሎቻቸውም መሆን ያስፈልገዋል። እግዚአብሔር ይባርካችሁ። ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...