የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ፤ 2ኛ ጢሞቲዎስ 2፤19

የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመፅ ይራቅ፤ 2ኛ ጢሞቲዎስ 2፤19

Engineers search the mass grave at the former mother and baby home in Tuam, County Galway.
ባለሙያዎች በመሬት ውስጥ የተቀበረውን በሚያይ ራዳር በመታገዝ Tuam, County Galway በሚባለው ና በአየርላንድ በሚገኝ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስር ይተዳደር የነበረ ያላገቡ እናቶች እና የህጻናት መኖሪያ ስፍራ ያለአገባብ ሞተውና አስከሬናቸው በአንድ ስፍራ በድብቅ የተቀበረ 800 የሚሆኑ ህጻናት አጽሞችን ሲመረምሩ

የወንጌል የምስራች እጅግ አስደናቂ እና ክቡር ዜና፣ ከዚህ በፊት ያልመጣ ከዚህም በኋላ ሌላ ምትክ የሌለው የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኃጢዓታችን እና በበደላችን የጠፋነውን እኛን የሰውን ልጆች ሊዋጅ የመጣው እግዚአብሔር ወልድ ነው። ይህ ከራሱ ከልዑል እግዚአብሔር ማደሪያ ከሰማይ የመጣው ዜና ደግመን ደጋግመን ብንሰማው፣ ብንዘምረው፣ ብንሰብከው ብንጽፈው የማይሰለች እውነት ነው። ይህን ታላቅ ዜና እንድናበስርና በወንጌሉ መዳን በሚገኘው አዲስ ሕይወት በመኖር የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ጽድቅና መልካምነት እንድናሳይ የተጠራን ደግሞ ራሳችንን ክርስቲያን ብለን የምንጠራ ሁሉ ነን። በእውነት ምስጢሩ ከገባን፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ተብሎ መጠራትን የሚተካከል ታላቅ ክብር፣ ሹመትና ኃላፊነት በዚህ ምድር ላይ የለም። ይህ ሥልጣን፣ ክብርና ኃላፊነት ግን በምድር ላይ እስከ ዛሬ ከነበሩ፣ ዛሬም ካሉና ነገም ሊመጡ ከሚችሉ ሹመቶችና፣ ክብሮችና ኃላፊነቶች ሁሉ የተለየ ነው። ምክንያቱም የዚህ ሥልጣን፣ ክብርና ሹመት ዋና ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን እንጂ ሰዎች እንዲያገለግሉት አይደለም። ስለዚህ፣ ባሪያ ከጌታው፣ ደቀ መዝሙርም ከመምህሩ አይበልጥምና የክርስቶስ ተከታይ ነኝ የሚል ማንኛውም ሰው እንደተሰጠው ጸጋ፣ ሹመትና ኃላፊነት መጠን በነገር ሁሉ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ሊከተል የግድ ነው። የክርስቶስ አገልጋይ ነኝ የሚል ሰው ደግሞ አገልግሎቱ በእግዚአብሔርና በሰዎች፣ እንዲሁም በሰማይ መላእክትና በጨለማው ዓለም ገዥዎችም ፊት ጭምር ስለሆነ ክቡር በሆነው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ላይ ነቀፌታን እንዳያመጣ በብዙ የእግዚአብሔር ፍርሃት መኖር ይገባዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው ሰዎች ሁሉ ኃጢዓትን ሰርተዋል፣ የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፣ ስለዚህም በኢየሱስ ክርስቶስ በተደረገው ቤዛነት በኩል ብቻ ከዘለዓለም ሞት ይድናሉ። ሮሜ 3፤23 ይህ መዳን የሚገኘው ደግሞ ሰው ኃጢአተኝነቱን ተገንዝቦ ንስሐ ሲገባና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በመሞት የከፈለውን የደህንነት ዋጋ በማመን የእግዚአብሔርን ጸጋ ሲቀበል ነው። አንድ ሰው ሰው ጌታን በማመንና በመቀበል የሚገኘውን ዳግም ልደት ከተለማመደ በኋላ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል በመመገብ፣ ለቃሉ በመታዘዝና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በእግዚአብሔር ጸጋ በማደግ ዕለት ከዕለት፣ ደረጃ በደረጃ ክርስቶስን እንዲመስል ወደሚያስችለው ሕይወት ለመድረስ መትጋት ያስፈልጋል። ለዚህም እድገት ደግሞ አንዱና ዋነኛው ማእከል የአማኞች ህብረት ወይም “ቤተ ክርስቲያን” ነው። አንድ ክርስቲያን እንደ አንድ ኩራዝ፣ ሻማ፣ ጧፍ፣ ፋኖስ፣ ማሾ፣ ወይም አምፖል የእግዚአብሔርን ብርሃን በኃጢዓት ጨለማ ውስጥ ላለው ዓለም ያበራል። ቤተ ክርስቲያንና የአማኞች ህብረት ደግሞ ብዙ ኩራዞች፣ ሻማዎች ወይም ፋኖሶች በተናጥል ከሚያበሩት በላይ ሊያበሩ ይችላሉ። ብርሃን ሊያበራ የማይችል ሻማ፣ ፋኖስ ወይም ኩራዝ ዋጋ ስለማይኖረው ምናልባት ለጌጥ ወይም ለአሻንጉሊትነት ካልሆነ በስተቀር ፈላጊ አይኖረውም። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማረውና ያስጠነቀቃቸውም ይህንኑ ነው። ጨው ጨውነት ከሌለው በስተቀር ድንጋይ ነው ተብሎ ወደ ውጭ ይጣላል በእግርም ይረገጣል። በተራራ ላይ የተሰራች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም፣ መብራትንም ስናበራ ለሰዎች ሁሉ በሚታይና በሚያሳይ ቦታ ላይ እናስቀምጠዋለን እንጂ ከእንቅብ በታች አናኖረውም። ማቴዎስ 5፡13-16
በዓለም መንግስታትም ሆነ በግል ድርጅቶች ሰራተኛ የሚሆኑ ሰዎች ሁሉ ለመንግስታቸውና ለድርጅታቸው ዓላማ፣ መልካም ስምና ተግባር ገንቢ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ቢያንስ ቢያንስ ግን አፍራሽ አስተዋጽኦ ማድረግ የለባቸውም። በነዚህ መንግስታትና ድርጅቶች እንደ ባለሥልጣን የሚሾሙ ደግሞ በተሰጣቸው ሥልጣንና ኃላፊነት መጠን የድርጅቱን ወይም የመንግስቱን ዓላማ ማራመድ እንዲሁም ደግሞ አፍራሽ ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች እንዳይፈጠሩ ጥንቃቄ በማድረግ ሌሎች ሰራተኞችን እና ባልደረቦቻቸውን የመምራት ግዴታ አለባቸው። ይህ የዓለም ሥርዓት ከሞላ ጎደልም ቢሆን ስለሚሰራ ነው በሰላም ወጥተን የምንገባው፣ ልጆች ወልደን የምናሳድገውና የምንኖረው። እነዚያ ባለስልጣናትና ሰራተኞች መልካም አድርገው ቢገኙ ይሾማሉ፣ ክፉ ካደረጉ ግን ውሎ አድሮም ቢሆን ይቀጣሉ፣ ሥልጣናቸውን ያጣሉ ወዘተ። የዚህ መልካም ሥርዓትና እውቀት ሁሉ ምንጭ ደግሞ እግዚአብሔር እንደሆነና ሥልጣንም ሁሉ የሚገኘው ከእርሱ እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንማራለን። ሮሜ 13፡1 ታዲያ የዚህ የሚያልፈው ዓለም መንግስታትና ድርጅቶች እንዲህ በመልካም አስተዳደር መሄድ ካስፈለጋቸው፣ የዓለም ብርሃን ናችሁ የተባሉ ክርስቲያኖች አካል የሆኑባት ቤተ ክርስቲያንማ እንዴት በላቀ መንገድ ልትኖር ይገባት !?
ሁሉ ድርጅት፣ ሁሉ ባለስልጣን ወይም ሁሉ መንግስት አንድ እንዳልሆነ እናውቃለን። መሆን ባይኖርበትም አብያተ ክርስቲያን ሁሉም የእግዚአብሔርን ቃል በአንድ መንገድ እንደማይረዱ ወይም ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ሁሉ መስራችና ባለቤት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን በአንድ ዓይነት መንገድ እንደማያንጸባርቁ ከታሪክም በዘመናችን ከምናየውም እንረዳለን። እያንዳንዱ በገዛ ፈቃዱ ክርስቲያን ነኝ ብሎ የሚያምን ሰውም ሆነ ቤተ ክርስቲያን ነኝ ብሎ የሚጠራ ድርጅት ሁሉ በአካሄዱ፣ በአስተዳደሩና በህብረተሰብ መካከል በሚያሳየው ባህርዩ ለክርስቶስ ወንጌል ምስክር ወይም እንቅፋት ሊሆን ይችላል። በክርስቶስ ያመነ ማንም ሰው፣ ከማይጠፋው ከእግዚአብሔር ቃል ዘር ተወልዶአልና ኃጢዓትን በፈቃዱና በተለምዶ ማስተናገድ አይችልም።  እግዚአብሔር ብርሃን ነውና ክርስቶስን የሚያምን በጨለማ ለመመላለስ አይችልም።

በዚህ ባያያዝኩት ዜና ላይ እንደምንመለከተው፣ ይህ ያለንበት ዘመን እጅግ አሳዛኝ፣ ዘግናኝ እና አሳፋሪ የሆኑ ዜናዎችን ከመስማት ልንሸሽ የምንችልበት ዘመን አይደለም። እያንዳንዳችን ክርስቲያኖች፣ ምንም ቦታ የለኝም የምንለውም ሆንን በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያለን ሁሉ በእኛ ላይ የሚጠራው የክርስቶስ ስም ከእኛም ሆነ የእኛ ከምንላቸው ነገሮችና ሰዎች በላይ መሆኑ ሁል ጊዜ በፊታችን ተቀርጾ ሊቀመጥ ይገባዋል። የክርስቶስ ተከታይ ነኝ የሚል ሰው እግዚአብሔርን ማመኑ፣ መከተሉና ማገልገሉ በምንም ዓይነት መንገድ ለዚህ ምድር ጊዜያዊ ኑሮ ማትረፊያ ወይም መጠቀሚያ ከመሰለው እጅግ ተሳስቶአል።1ኛ ጢሞቲዎስ 6፡5-10። እንኳን  አገልጋይና የቤተ ክርስቲያን መሪ ይቅርና እያንዳንዱ ተራ ክርስቲያንም ቢሆን በክርስቶስ ያለውን ነጻነትና መልካም ስም ለክፋት መሸፈኛ ማድረግ የለበትም። 1ኛ ጴጥሮስ 2፡16። ወገኖች የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ሩቅ አይደለም። እሱ ሲመጣ ደግሞ ለእያንዳንዱ እንደ ስራው ዋጋውን ይሰጣል። ልንገነዘብና ልንፈራ የሚያስፈልገን ግን አንድ ቁም ነገር አለ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማይ መላእክቱ ጋር በክብር ሲገለጽ፣ የክርስቲያን ስም በላያችን ላይ ለጥፈን በውስጣችን፣ በዙሪያችንና በኃላፊነት ቦታችን አውቀን፣ ፈልገን የሸሸግነው ነውር እንዳይገኝብን እንጠንቀቅ። እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያደላም። የክርስቲያን ስም ወይም የሹመት ማእረግ መያዛችን የኃላፊነታችን ቀንበርና ምልክት እንጂ የፈለግነውን ሁሉ እያደረግን እና እንዳሻን እየተመላለስን ምንም አልሆንም ብለን የምንኩራራበት ምሽግ አይደለም። ኃጢዓት እግራችንን ጠልፎ ሊጥል ሁል ጊዜ በዙሪያችን፣ በሃሳባችን፣ በምንሰማው፣ በምናየው፣ በምናነበው ነገር ሁሉ ውስጥ ያደባል። ነገር ግን ጌታ ለቃየል እንደነገረው፣ እግዚአብሔርን በመታዘዝ ልንቃወመውና በእግራችን ስር ልንረግጠው ስልጣን አለን።  “ጌታ ለእርሱ የሆኑትን ያውቃል፥ ደግሞም የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ከዓመጽ ይራቅ የሚለው ማኅተም ያለበትና የተደላደለ የእግዚአብሔር መሰረት ቆሞአል።” 2ኛ ጢሞቲ 2፤19። ወንድማችሁ ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...