የሰው ልጅ መንፈሳዊ ታሪክ ምስጢር ከኖኅ እስከ ባቢሎን፣ ከባቢሎን
እስከ እስራኤል፣ ከእስራኤል እስከ ቤተ ክርስቲያን መመስረት፣ ከቤተ ክርስቲያን እስከ እስራኤል መሰብሰብና እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት
ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሱ።
ሉቃስ 21:28
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የዳግም
ምጽዓቱን መቃረብ እንደሚያመለክቱ ከሰጣቸው ምልክቶች ውስጥ አንዱንና ትልቁ በዓለም ላይ የሚታየው ሁኔታ ከጥፋት ውኃ በፊት ቀደም ብሎ ኖህ ወደ መርከብ እስገባበት ቀን ድረስ በምድር ላይ የነበረውን
መንፈሳዊ፣ ሞራላዊ፣ ህብረተሰባዊ፣ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ውድቀትን እንደሚመስል ነበር። እነዚህ ነገሮች ደግሞ በቀደሙት መልእክቶች
ላይ ተመልክተናል። ይህን የዛሬውን መልክት ለመረዳት ደግሞ እነዚያን ስለ ኖኅ ዘመን የተማርናቸውን ማንበብ ያስፈልጋል።
በኖኅ ዘመን ከልኩ አልፎ
የገነፈለው መንፈሳዊና ሞራላዊ ውድቀት እጅግ የከፋና ከመቤዠትም ያለፈ ስለነበር ጌታ አምላክ የዚያን ዘመኑን ዓለም በውሃ አጠፋ።
ጌታ አምላክ ከዚያ ጥፋት በኖህ መርከብ አማካይነት የዳኑትን 8 ሰዎችና የተመረጡ እንስሳት ባርኮ ምድር ሁሉ እንደገና በሕያዋን
ፍጥረታት ተሞላች። እጅግ የሚያሳዝነው ግን ከዚያ ከጻድቅ ሰው ከኖኅ ዘር የወጡት የሰው ልጆችም ቢሆን እንደገና አመጹ። አባቶቻችንና
እናቶቻችን ክርስቲያኖች ስለሆኑ ወይም ጻድቃን ስለነበሩ እኛ በነሱ ትኬት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አንገባም። የኖኅ ልጆች ከሌሎች
ከወደቁት ከሰማይ መላእክት ጋር በዓመጽ በመተባበር የፍጥረትን ሁሉ አምላክ እግዚአብሔርን በመተውና “ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ
እንስራ” በማለት የልዑል አምላክን ሥልጣንና ሥርዓት የሚጋፋና የሚያፈርስ የዓለም ሥርዓት ለመመስረት በናምሩድ አስተባሪነት ተሰበሰቡ።
ይህ ዓመጽ የተፈጸመበትን በሰናዖር (SHINAR) ሜዳ ያለ ስፍራና የተካሄደውን ዓመጽ መጽሐፍ ቅዱስ ባቢሎን ይለዋል። በዚህ በባቢሎን
ጊዜ ግን ጌታ እግዚአብሔር የሰዎችና የኔፊሊም ዓመጻ ወደ ፍሬያማነት ደረጃ እንዲደርስ አልፈቀደም። ወደነበሩበት ስፍራ ከመጣና የአካሄዳቸውን
የጥፋት አቅጣጫ ከተመለከተ በኋላ ስራቸው ወደግቡ እንዳይደርስ ቋንቋቸውን ደባለቀ፣ የጀመሩትንም ከተማና ሥራ ትተው እንዲሄዱ በምድር
ሁሉ በተናቸው። በዘፍጥረት 11 ቁጥር 8 ላይ “እግዚአብሔርም ከዚያ በምድር ሁሉ ላይ በተናቸው፣ ከተማይቱንም መስራት ተው።” ይላል።
ከብዙ ዘመናት የታሪክና የአርኪዎሎጂ ጥናት በኋላ ያች ስራዋ ሳይጠናቀቅ የተተወች የሰናዖር ሜዳ ከተማ ኤሪዱ (ERIDU) የተባለች
መሆኗን እና ይችም ከተማ የሰው ልጆች ከሰሯቸው ከተሞች ሁሉ የመጀመሪያይቱ ልትሆን እንደምትችል የመጽሐፍ ቅዱስ፣ የታሪክና የአርኪዎሎጂ
ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።
በባቢሎን ዘመን ጌታ አምላክ
ያደረገው የሰዎችን ቋንቋ መደባለቅ ብቻ አልነበረም። ፍላጎታቸው ከሱ በታች የሆኑ ፍጥረታትን፣ ማለትም የወደቁ መላእክትን፣ የነሱን
ልጆች አጋንንትንና ሌሎችንም የሰማይና የምድር ፍጥረታትን ማምለክ ስለነበረ ጌታ አምላክ እነሱ ካልፈለጉት በቀጥታ በእርሱ ሥር ይተዳደሩ ከነበረበት ሥርዓት ስር አውጥቶ እነሱ በመረጡት በሉሲፈርና በወደቁት
መላእክቱ አስተዳደር ሥር አደረጋቸው። ይህንንም ሲያደርግ በዚያን ዘመን የነበሩትን ህዝብ በነገዶች መሪዎቻቸው ቁጥር ሰባ
(70) ቦታ ላይ በመክፈልና በእያንዳንዱም ላይ የሚያስተዳድሩ የሰማይ መላእክትን በመሾም ነበር። እነዚያ ሰባዎቹን የምድርን ወገኖች
የሚያስተዳድሩ የሰማይ መላዕክትም ስማቸው ጠባቂዎች (ወይም WATCHERS) እንደሚባሉ መጽሐፍ ቅዱስ ያሳያል። በዘፍጥረት ምዕራፍ
10 ላይ የተገለጠው የአህዛብ ወይም የምድር ህዝቦች ሊስት ሰባ (70) የጎሳ ወይም የዘር መሪዎችን የያዘ ነው። እነዚህ ሰባዎቹ
ነገዶች ናቸው በቀጥታ በጌታ እግዚአብሔር ስር በመተዳደር ፈንታ እነሱ ራሳቸው እንደፈለጉት በወደቀው ኪሩብ በሉሲፊር ስር በነበሩት
በጠባቂ መላእክት (WATCHERS) እንዲተዳደሩ የተደረጉት።
በኋላ ከተጠራውና የእግዚአብሔር
ርስት ለምትሆነው ለእስራኤል አባት ከሆነው ከአብርያም በስተቀር ከነዚያ ከሰባዎቹ ነገዶች ውስጥ በሰማይ ጠባቂዎች
(WATCHERS) ስር ያልተደረገ ማንም ሕዝብ አልነበረም። ኦሪት ዘዳግም 32 ቁጥር 8 ይህንኑ የጌታ አምላክን ውሳኔ እንዲህ ሲል
ያስረዳል። “የዱሮውን ዘመን አስብ፥ የብዙ ትውልድንም ዓመታት አስተውል፥ አባትህን ጠይቅ ያስታውቅህማል፣ ሽማግሌዎችህን ጠይቅ ይነግሩህማል።
ልዑል ርስታቸውን ለአህዛብ ባወረሰ ጊዜ፣ የአዳምን ልጆች በለየ ጊዜ፣ እንደ እስራኤል ልጆች ቁጥር፣ የአህዛብን ድንበር አቆመ።
የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ህዝቡ ነው፥ ያዕቆብም የርስቱ ገመድ ነው።” እነዚያን የሰማይ ጠባቂዎች (WATCHERS) ወይም በሰይጣን
ሥር ሆነው አህዛብን እንዲያስተዳድሩ የተመደቡትን የወደቁትን መላእክትን እና ልጆቻቸውን ኔፊሊምን ነው የሰው ልጆች የአገራችን አማልክት
እያሉ ያመልኩአቸው የነበረው። ለምሳሌ የሞዓባውያን አምላክ ኪሞሽ፣ የአሞናውያን አምላክ ሞሎክ፣ የባቢሎን አማልክት ማርዱክ፣ በዖልና
ብልጣሶር ወዘተ ነበሩ። ለዚህም ነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ስፍራ
ላይ አገሮችንና ህዝቦችን የሚገዙ በአየር ላይ ሥልጣን ያላቸው ገዢዎች እንዳሉ የሚናገረው። ለምሳሌ ዳንኤል 4:13 ፣ 4:17 ፣
4:23 ፣ ዳንኤል 10:13 እስከ 21፣ ማቴ 4:9፣ ሉቃስ 4:6፣ ኤፌሶን 6:12 ፣ ዮሐንስ 14:30 ፣ ዮሐንስ 12:31 ።
ለዚህም ነው ዲያብሎስ ጌታ ኢየሱስን በምድረ በዳ በፈተነው ጊዜ የዓለምን መንግስታትና ክብራቸውን ለጌታ ለኢየሱስ አሳይቶ ይህ ሁሉ
የኔ ነው፣ ከሰገድህልኝ ላንተ እሰጥሃለሁ ያለው። ዲያብሎስ ይህንን ሲናገር ታዲያ ከመጀመሪያውም የዓለም መንግስታት በሱ ስር እንዲሆኑ
የሰጠው ያ ሊፈትነው የቀረበው ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አላወቀም ነበር። ለዚህ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ የአሁኑ ዘመን የምድር ገዥዎች
የእውቀትን ራስ አላወቁትም። ቢያውቁ ኖሮስ አይገድሉትም ነበር ያለው። ምክንያቱም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣንን ድል የነሳው በመስቀል
ሞቱ ነው። ሰይጣንና የሚከተሉት የወደቁት መላእክቱ በባቢሎን የሰውን ዘር እንዲያስተዳድሩ ስለተመደቡም ነው ጌታ ኢየሱስ ሰይጣንን
የዚህ ዓለም ገዢ ብሎ በወንጌል ላይ የጠራው። ጌታም በመጨረሻ ወደ
መስቀሉ ሲሄድ የዚህ ዓለም ገዢ ተፈረደበት ወይም ተጣለ አለ። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለ ተቀበሉ ሰዎች
ሁሉ ሲናገር “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፣ ቤዛነቱንም እርሱም የኃጢዓትን
ሥርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት አፈለሰን።” ቆላስይስ 1:13 የሚለው።
ጌታ አምላክ የአህዛብን
የልባቸውን ዝንባሌና ፍላጎት፣ እንዲሁም በተግባር በተደጋጋሚ ያደረጉአቸውን ምርጫዎች ከተመለከተ በኋላ የፈለጉትን ሰጣቸው እንጂ
እሱ ራሱ ደግሞ የሁሉም አምላክ ነውና እነዚያ ጠባቂዎች (WATCHERS) የተባሉትና በሉሲፈር ስር የሚተዳደሩት መላእክት ደግሞ
እንደፈለጋቸው እንዳይፈነጩ ለስልጣናቸው ገደብን አደርጎለታል። ለምሳሌ አንድ ሰው የነዚህን የጠባቂዎችን የክፋት መንገድ አልከተልም
ብሎ እና ጌታ አምላክን ወዶ በጽድቅ ቢመላለስ ጠባቂዎቹ ያንን ሰው እነሱ እንደሚፈልጉት እንዲሆን ሊያስገድዱት አይችሉም። ከጌታ
አምላክ ካልተፈቀደላቸው በቀር መከራና ፈተናንም እንኳን ሊያመጡበት አይችሉም። ይህንን በተመለከተ የኢዮብን ታሪክ በሚገባ ማስተዋል
ያሻል። ኢዮብ ላይ የደረሰውን መከራ ብቻ ሳይሆን፣ ከመከራው በፊት ጌታ አምላክ በሚመራው በሰማይ ጉባኤ የተካሄደውን የክስና የፍርድ
ስርዓት በተመለከተ በኢዮብ ምእራፍ 1 ቁጥር 7 እስከ 12 እና ምእራፍ 2 ከ1 እስከ 6 ያለውን በሚገባ እናስተውል። ለዚህ ነው
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በአማልክት ላይ አአምላክ ነው፣ በአማልክት ጉባኤ መካከል ይፈርዳል የሚለው። ለምሳሌ መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ
82 ቁጥር 1 እስከ 8ን አንብቡ። ስለዚህ አህዛብን እንዲገዙ ያስቀመጣቸውን ሰማያዊ ጠባቂዎችንም (WATCHERS) የሚገዛውና የሚፈርድባቸው
የእስራኤል አምላክ፣ የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር ነው። በዚህ በመዝሙረ ዳዊት 82 ላይና በሌሎችም ብዙ ስፍራዎች
እንደምናነበው እነዚያ ጠባቂዎች ደግሞ በሚገባ ስላላስተዳደሩ፣ ጻድቃንን በማሰቃየት ለአመጸኞች ስለፈረዱና ራሳችውም በሙስና ውስጥ
ስለተዘፈቁ ምንም እንኳን አማልክት ቢሆኑም እንደሚፈረድባቸውና እንደሚሞቱ ይናገራል። የእሳት ባህርም የተዘጋጀው ለነዚህ ክፉ ገዢዎችና
ለአለቃቸው ለዲያብሎስ ነው። በነዚህ ላይ ነው ሐዋርያው ጳውሎስ “በመላእክት ላይ እንኳን እንድንፈርድ ዘንድ እንዳለን አታውቁምን?
“ ብሎ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን የጻፈው። 1ኛ ቆሮ 6:3ን ተመልከቱ። እነዚህ ጠባቂዎች ናቸው ዛሬም ቢሆን የምድርን
አህዛብ ከመንግስታት ጀርባና ከበላያቸው ሆነው የሚገዙትና የሚያስቷቸው።
ለዚህ ነው የእግዚአብሔር ቃል ለመንግስታት መሪዎችና በስልጣን ላይ ላሉ ሁሉ ጸልዩ ብሎ የሚያዝዘን። 1ኛ ጢሞቲዎስ 2:2ን ተመልከቱ።
እነዚህ የአሁኑ ዓለም ገዢዎች ሳይወዱ በግድ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይፈጽማሉ። ብዙ ጊዜ ግን በዓመጽ የራሳቸውን ክፉ ሃሳብ ለማድረግ
ሲሞክሩና የሰው ልጅም በአካሄዱና በምርጫው ሲተባበራቸው ምድር ቀውስ ውስጥ ትገባለች። ለዚህ ነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናንተ
የምድር ጨውና የዓለም ብርሃን ናችሁ ብሎ ለደቀመዛሙርቱና ክርስቲያን ነን ለምንል ሁሉ ያስተማረው።
አህዛብን በጠባቂዎች ስር
ያኑር እንጂ ጌታ አምላክ ለሱ ለራሱ ደግሞ እስራኤልን አስቀርቶ ነበር። አብርሃምን ወደራሱ ጠርቶና ፈትኖ ቃል ኪዳን ከገባለት በኋላ
እውነተኛና መንፈሳዊ የሆነው የአብርሃም ዘር የእግዚአብሔር ርስት ሆነ። ለዚህ ነው ጌታ አምላክ እስራኤልን ከግብጽ ባርነትና ከፈርዖን
ስልጣን ስር ነጻ ያወጣው። የግብጽ ፈርኦኖች አማልክት ናቸው ተብለው የሚመለኩና ብዙዎቹም ከኔፊሊም ጋር የተያያዘ ሰማያዊ ዘር አለን
የሚሉ ነበሩ። ለዚህ ነው የግብጻውያን መሪዎች የእስራኤልን ህዝብ የበኩር ልጆች ገና ሲወለዱ በመግደልና ከዚያም የተረፉትን ወደ
አባይ ወንዝ በመጣል ሊያጠፉአቸው የተነሱት። ለዚህ ነው ጌታ አምላክ ራሱ ከእስራኤል ልጆች ጋር በመውጣትና የፊቱን መልአክ በመላክ
እስራኤላውያን በከነዓን ምድር የነበሩትን የኔፊሊምን ዘር እያጠፉ ምድሩን እንዲወርሱ የረዳቸው። በጌት የነበረውና ዳዊት የገደለው
ጎልያድ የኔፊሊም ዘር ቅሪት ነበር። ኢያሱ ምድሩን ለእስራኤል ሲያወርስ ሳያጠፋቸው የቀሩ የኔፊሊም ዘሮች ሸሽተው የሰፈሩባቸው ቦታዎች ጌት፣ ጋዛና አዛጦን ነበሩ። እስራኤል በልዑል አምላክ ስር በቀጥታ የሚተዳደሩ
ብቸኛና ቅዱስ ሕዝብ፣ የንጉስ ካህናት፣ ምርጥ ህዝብና ለአህዛብ ብርሃን እንዲሆኑ የተጠሩ ስለነበሩ ነው ከሌሎቹ ከአካባቢያቸው አህዛብ
ጋር በአምልኮ፣ በጋብቻና በአኗናሯቸውም ሳይቀር እንዳይደባለቁ የታዘዙት። ያንን ካደረጉ ሳይወዱ በግድ እነዚያን አህዛብን በሚገዙት
ጠባቂዎች ስልጣንና የአጋንንት አምልኮ ኃይል ስር እንደሚወድቁ ጌታ አስጠንቅቋቸው ነበር። ይህ እጅግ ታላቅ የሆነ መንፈሳዊ ምስጢር
እንጂ የዘረኝነት ወይም የአንድ ዘር ከሌላው የመሻል ጉዳይ አይደለም። ጌታ አምላክ ራሱ ይህንን ለእስራኤል በግልጽ ሲነግራቸው የመረጣቸው
ከአህዛብ ሁሉ ይልቅ ሰለሚሻሉ ወይም በቁጥር ስለበዙና ኃይለኛ ስለሆኑ ሳይሆን ከአባቶቻቸው ጋር ስላደረገው ቃል ኪዳን የተነሳ ስለወደዳቸው
መሆኑን አስታውቆአቸዋል። ዘዳግም 7 ቁጥር 7 እና 8።
እስራኤል ማለት በአካል
የያእቆብ ልጆች የሆኑትን የአስራ ሁለቱን ነገዶች ዘር የሚጠቅስ ሲሆን በመንፈስ ደግሞ የአብርሃምን የእምነቱን ፍለጋ የሚተከተሉት
ሁሉ ናቸው። ሮሜ 4:12 በብሉይ ኪዳን ዘመን እግዚአብሔር ራሱ ነበር እስራኤልን በቀጥታ የሚያስተዳድራቸው። ለዚህ ነው እስራኤል
የበኩር ልጄ ነው ብሎ ጌታ የተናገረው። ዘጸዓት 4:22። ለዚህ ነው እስራኤልን ለማዳን ጌታ አምላክ ማንኛውንም ህዝብና ገዢ ያንበረክክ የነበረው። ማንኛውም የአብርሃም ዘር የአባታቸውን የአብርሃምን
የእምነቱን ፍለጋ በመከተል የአብርሃምን፣ የይስሐቅንና የያዕቆብን አምላክ ካመለኩና ከተከተሉ፣ ከሌሎች የአህዛብ አማልክት አምልኮና
ተጽእኖ ከተጠበቁ የእግዚአብሔር ሕዝብና ርስት ናቸው። አንድ ሰው በስጋ የአብርሃም ዘር ሆኖ የእስራኤልን አምላክ ካላመነና ካልታዘዘ
መንፈሳዊ እስራኤል አይደለም። በዘሩ የአብርሃም ዘር ያልሆነ ሰው ደግሞ በእውነትና በመንፈስ አብርሃም ያመነውንና የታዘዘውን አምላክ
ቢያምን፣ ቢታዘዝና ቢከተል በስጋ እስራኤላዊ ባይሆንም እንኳን በመንፈስ ግን የአብርሃም ልጅ ይሆናል። ይህ በብሉይ ኪዳን ዘመንም
ሆነ በአዲስ ኪዳን እውነት ነው። ለምሳሌ የኢያሪኮይቱ ጋለሞታይቱ ረዓብና ሞአባዊቷ ሩት ዋና ዋና ምሳሌዎች ናቸው። እጅግ ብዙ እስራኤላውያን
ጌታ አምላክን ታዝዘው ቢኖሩም ብዙዎቹ፣ በተለይም ደግሞ መሪዎቻቸው እግዚአብሔርን ስላልታዘዙ፣ በመጨረሻም ደግሞ በአካል በመካከላቸው
የተገለጸውን የእግዚአብሔርን ልጅ፣ እውነተኛውን መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስን በአገር አቀፍ ደረጃ ስላልተቀበሉት ከእግዚአብሔር ጋር
የገቧቸውን ቃል ኪዳናት አፈረሱ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሳና ካረገ በኋላ ያመኑት ደቀመዛሙርት (እስራኤላውያን የሆኑ)
ወንጌልን ለምድሩ ሁሉ ስለሰበኩ ብዙ እስራኤላውያን በመሲሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቢያምኑም በአገር ደረጃ ግን እስራኤል ስላልተቀበሉትና
ከጌታ ትንሳኤ በኋላ የተሰጣቸውንም 40 ዓመት የንስሃ ጊዜ ስላልተጠቀሙበት
በሮማዊው ቲቶ (TITUS) ይመራ የነበረው የአህዛቡ የሮም ሰራዊት ኢየሩሳሌምን አፈራርሶ፣ የእስራኤል መንግስትነት ለጊዜው አብቅቶ፣
የቀሩት አይሁድ በምድር ሁሉ ተበተኑ። ወንጌልን በመጀመሪያ ለምድር ሁሉ ያበሰሩትም እስራኤላውያንና አይሁድ የነበሩ ሐዋርያት መሆናቸውን
አንዘንጋ። ጳውሎስ በሮሜ መልእክት ላይ እንደጻፈውና ነቢያትም ከዚያ በፊት እንደተናገሩት እስራኤል ምንም እንኳን የቃል ኪዳን ልጆችና
የተስፋው ቃል ወራሾች ቢሆኑም፣ እንደ አገር መሲሁን ኢየሱስን ባላመቀበላቸው መንፈሳዊ ድንዛዜ ሆነባቸው። ሮሜ ምእራፍ 9፣ 10
እና 11ን ተመልከቱ። ስለዚህም ከዚህ መንፈሳዊ ድንዛዜ እስኪነሱ ድረስ ወንጌል ለአህዛብ ሁሉ ባለፉት ሁለት ሺ ዓመታት ተሰበከ።
በመጨረሻው ዘመን ግን እስራኤል ከመንፈሳዊ ድንዛዜአቸው ተነስተው ጌታ ኢየሱስን እንደሚቀበሉት ነቢዩ ዘካርያስ ጽፎአል። ዘካርያስ
12:10 ስለዚህ እግዚአብሔር እስራኤልን በትኖ በቤተ ክርስቲያን ተክቷል የሚለው ትምሕርት የተሳሳተና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ነው።
ጌታ ኢየሱስ ስለዳግም ምጽዓቱ
ከሰጠን ምልክቶችም አንዱ “በለስ ስታቆጠቁጥ ጫፍዋም ሲለሰልስ ያን ጊዜ በጋ እንደቀረበ ታውቃላችሁ” ማቴ 24:32 የሚለው ስለ እስራኤል እንደ አገር ተመልሶ መመስረት የተነገረ ትንቢት ነው። በብሉይ ኪዳንም ብዙ ነቢያት እስራኤል ከመበተን በኋላ እንደገና
አገር እንደምትሆንና በእስራኤልም መዳን ለዓለም ሁሉ የወንጌል መሰበክ ተደምድሞ የጌታ መንግስት በምድር ላይ እንደምትገለጥ ተናግረዋል።
ታዲያ በ70 ዓም ኢየሩሳሌም ስትፈርስ ተበትኖ የነበረው የአይሁድ ህዝብ ከ2000 ዓመታት ያህል በኋላ ከምድር ሁሉ ተሰብስቦ ያች
የጥንቷ እስራኤል ጌታ አምላክ ለአብርሃም ቃል በገባለት መሰረት ምድር ላይ እንደገና አገር ሆና የተመሰረተችው ባለፈው ምዕተ ዓመት
በ1948 እ ኤ አ ነበር። ይህ አስገራሚና አስደናቂ ተአምራት ጌታ ኢየሱስ ዳግም የሚመለስበት ዘመን መቃረቡን ያለጥርጥር ከሚያስረዱን
ክስተቶች አንዱና ዋነኛው ነው። የዛሬዋ እስራኤል ዜጎች ብዙዎቹ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አያምኑም። የሚያምኑ ብዙ ግን አሉ። እግዚአብሔር
ሕዝቡን እስራኤልን እንደገና ሰብስቦ አገሪቱ የተመሰረተበትን ዋና ዋና ምክንያቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ስናስተውል የሚከተሉትን አምስት
ነጥቦች ማመልከት እንችላለን 1ኛ) እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባውን ቃል ኪዳን እስከመጨረሻ የሚጠብቅ አምላክ መሆኑን ለማሳየት
ነው 2ኛ) እስራኤል በመጀመሪያ ለነሱ የመጣውን ወንጌልን እንደገና እንዲሰሙና በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው እንዲድኑ የእግዚአብሔር
ፈቃድ ነው 3ኛ) አህዛብ ሁሉ የእስራኤል አምላክ እሱ ብቻ አምላክ እንደሆነ እንዲያውቁ፣ እንዲያምኑና እንዲድኑም ይሻል 4ኛ) በሰማይም፣
በምድርም፣ ከምድርም በታች ያሉ ሁሉ ስልጣን የእግዚአብሔር ብቻ መሆኑን እንዲያውቁ ነው 5ኛ) በልጁ በክርስቶስ በኩል በዓለም ሁሉ
ላይ የሚፈርድበትንና የዘለዓለም መንግስቱን ለመግለጥ ጊዜው መዳረሱን ለማመልከት ነው።
እስራኤል ዛሬ እውን የሆነች
አገር ነች። ይህ እውነት የምድር አህዛብ፣ የሲኦል አጋንንትና ግዑዛን ፍጥረታትም ሁሉ ቢያብሩ ሊቀየር የማይችል ነገር ነው። ይህን
የማይቀበሉና እስራኤልም በቆዳ ስፋትና በህዝብ ብዛት ትንሽ መሆኗን ተመልክተው ሊያጠፉአት የሚፈልጉ የምድር መንግስታትና ህዝቦች ቢኖሩም የእግዚአብሔርን ኃይልና
የእስራኤልን ታሪክ በሚገባ ያልተገነዘቡ ናቸው ናቸው። ለዚህም ነው ታላላቅ ነን የሚሉትን የዓለም መንግስታት ጨምሮ ብዙ አህዛብ
በእስራኤል ላይና በኢየሩሳሌም ላይ እየተነሱ ያሉት። ጠፍታለች፣ ወድማለች፣ ሁለተኛ አትነሳም የተባለች አገርና ሕዝብ ከ2000 ዓመት
በኋላ ተሰብስበው አገር መሆናቸውና ይህ ደግሞ በ20ኛው እና በ21ኛው ክፍለ ዘመን መፈጸሙ ራሱ ታላቅ ተአምራትና የመጽሐፍ ቅዱስ
ትንቢት ፍጻሜ መጀመሪያ ነው። ዓይናችን እያየ ትንቢት እየተፈጸመ ነው። የእግዚአብሔር ቃል በሙሉ ይፈጸማል። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ
ተመልሶ ይመጣል። ስልጣንና መንግስት ሁሉ ወደባለቤቱ ወደ ልዑል አምላክ
ይመለሳል። ለጊዜው ጨለማ ያንዣበበ ይምሰል እንጂ፣ እግዚአብሔርን ለሚፈሩትና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑት ሁሉ የጽድቅ ጸሃይ
በክንፎችዋ ፈውስን ይዛ ትወጣለች። ስለዚህ ቤዛችን የሆነው የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መገለጥ በደጅ ነውና አሻቅበን ራሳችንን በማንሳት
በደስታ ልንቀበለው ተዘጋጅተን እንኑር።
ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ