የእግዚአብሔር መለከት ድምጽ ይሰማናል ወይ?

የእግዚአብሔር መለከት ድምጽ ይሰማናል ወይ?
ከማንኛውም ድምጽ ከሚያወጣ መሳሪያ ይልቅ መለከት ወይም ቀንደ መለከት በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ትልቅ ስፍራ ተሰጥቶት እናያለን። በገና፣ ከበሮ፣ እንቢልታ፣ ጸናጽል እና ሌሎች መሳሪያዎች እግዚአብሔርን ለማምለክ በስራ ላይ ውለዋል። መለከት ግን ለአምልኮ፣ ለንስሃ ጥሪ፣ ለነጻነትና ለኢዮቤልዩ ማወጃ፣ ለንግሥና አዋጅ፣ ለማስጠንቀቂያና ለጦርነት መጥሪያ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ድል ለማመልከትና በመጨረሻም የልዑል እግዚአብሔርን ፍርድ ለማመልከት በስራ ላይ ውሏል። ቀንደ መለከት ከበግ ቀንድ የተሰራ ሲሆን ጌታ እግዚአብሔር ራሱ ሙሴን ሥራ ብሎ ያዘዘው መለከት ግን ከብር የተሰራ ነበር። ዘሆልቁ 10:1 እስከ 7 ተመልከቱ። ራሱ ጌታ እግዚአብሔር ነው ሙሴ ሁለት የብር መለከቶች እንዲሰራ ያዘዘው። እነዚህንም መለከቶች ሙሴ ይጠቀምባቸው የነበረው ከግብጽ የወጣውን የእግዚአብሔርን ህዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ወደሚገናኙበት የመገናኛው ድንኳን ለመጥራት፣ በበረያው ጉዞአቸውም የሚነሱበትንና የሚያርፉበትን ሥርዓት ለማስተማርና መልእክት ለማስተላለፍ ነበር።
መለከት በእስራኤል ብቻ ሳይሆን በሰማይም ሥራ ላይ እንደሚውል መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። የዮሐንስ ራእይ በመለከቶች የተሞላ ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም በክብር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ በሰማይ መላእክትና በቅዱሳን ታጅቦ ሲሆን ይህንንም ለማወጅ የመላእክት አለቃ ድምጹን ያሰማል ፍጥረት ሁሉ የሚሰማው የእግዚአብሔርም መለከት ይነፋል። 1ኛ ተሰሎንቄ ምእ 4 ቁጥር 13 እስከ 18 ተመልከቱ። የራዕይን መጽሃፍ ያስተላለፈልን ሐዋርያው ዮሐንስም በመንፈስ ሳለ በፍጥሞ ደሴት ላይ ጌታ ሲገለጥለት የሰማው የመለከትን ድምጽ ነበር። መለከት ሲነፋ ስርዓትና መልእክት አለው። በዘሆልቁ ምእራፍ 10 ላይ ለምሳሌ ጌታ ሙሴ እንዴት መለከቱን መንፋት እንደነበረበትና ህዝቡም መልእክቱን እንዴት መስማትና መተርጎም እንደሚገባቸው አስተምሮታል። ለኛ ለዛሬ ክርስቲያኖች ደግሞ ጌታ ኢየሱስ በዮሐንስ ወንጌል ምእራፍ 10 ቁጥር 27 እስከ 30 ላይ “በጎቼ ድምጼን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፥ እኔም የዘላለም ህይወትን እሰጣቸዋለሁ ለዘላለምም አይጠፉም፣ ከእጄም ማንም አይነጥቃቸውም። የሰጠኝ አባቴ ከሁሉ ይበልጣል፣ ከአባቴም እጅ ሊነጥቃቸው ማንም አይችልም። እኔና አብ አንድ ነን።ብሎናል ታዲያ የጌታን የኢየሱስን ድምጽ እየሰማን ነው ወይ። ድምጹን የምንሰማው ቃሉን (መጽሐፍ ቅዱስን) ስናነብ፣ ስንጸልይ እና የተማርነውን ደግሞ በስራ ላይ ስናውል ነው። 
ወገኖች፣ የጌታ ኢየሱስ መምጣት እጅግ ተቃርቧል። በዚህ ቀን በዚህ ዓመት ይሆናል ብለን ቀጠሮ መቅጠር ስህተት ነው።  ያለንበት ዘመን ምልክቶች ሁሉ የሚያሳዩት ግን ዘመኑ እንደተቃረበነው። ኑሮአችንን መኖሩን እንቀጥል ግን ከጌታ ጋር ላለን ግንኙነትና ህብረት ደግሞ ቅድሚያ እንስጥ። በኖህ ዘመን እንደነበሩ ሰዎች የጌታ መምጣት እንዳይደርስብን ነቃ ብለን እንኑር። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ለነበሩ ክርስቲያኖች ከሁለት ሺ አመታት ያህል በፊት ሲጽፍ እንኳን ቀኑ እንደቀረበ ተናግሮ ነበር፣ ታዲያ በኛ ጊዜማ ምን ያህል የጌታ መምጣት የበለጠ ይቃረብ?? የቃሉ መለከት ድምጽ እንዲሰማን ከዚህ ዓለም የኑሮ እንቅልፍና ሰመመን እንንቃ !!

ከእንቅልፍ የምትነሱበት ሰዓት አሁን እንደደረሰ ዘመኑን እወቁ፤ ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና። ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአልና። እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ። ሮሜ 13፤11፡12

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...