ወገባችሁ የታጠቀ መብራታችሁም የበራ ይሁን፣ እናንተም ጌታቸው መጥቶ ደጁን ሲያንኳኳ
ወዲያው እንዲከፍቱለት ከሰርግ እስኪመለስ ድረስ የሚጠብቁ ሰዎችን ምሰሉ። ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች
ብጹዓን ናቸው፤ እውነት እላችኋለሁ ታጥቆ በማዕድ ያስቀምጣቸዋል፥ ቀርቦም ያገለግላቸዋል። ….. እናንተም ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና። ሉቃስ 12:35-40
ሁሉን ነገር ዛሬውኑ ልያዘው፣
ልጨብጠው በሚባልበት በዚህ ዘመን እንደ መጠበቅ ከባድ ነገር የለም። በተለይም ደግሞ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ብልጽግናና የቴክኖሎጂ እድገት
ላይ በሚገኙት አገሮች ውስጥ ዛሬ መጠበቅ እንደ ትልቅ መከራ ይቆጠራል።
ኑሮ ከድመት ወይም ከሌሎች አደጋዎች ለማምለጥ የሚራወጡትን የአይጦች ውድድር ይመስላል። በርግጥም ደግሞ ይህንን ገደብ የለሽ ሩጫ
ፈረንጆቹ የአይጥ ውድድር ወይም RAT RACE ይሉታል። ያላገኘ ለማግኘት፣ ያገኘ ደግሞ ባለው ላይ ለመጨመርና ያለውንም እንዳያጣ
ለመጠበቅ ይዋከባል። እስቲ የመገናኛ እና የመረጃ መለዋወጫ መሳሪያዎችንና መረቦችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የዛሬ አርባ አመት ገደማ
በሰዎችም ሆነ በድርጅቶች መካከል ዋነኛው የመረጃ መለዋወጫ መንገድ ደብዳቤ መጻጻፍ ነበር። በአገራችን በኢትዮጵያ 15 ሳንቲም ከፍለን
ደብዳቤ ጽፈን የምንልክባት እንደ ፖስታም፣ እንደወረቀትም እንደ ቴምብርም የምታገለግል ኤሮግራም የምትባል አንድ ፖስታ ቤት የሚሸጣት
ወረቀት ነበረች። ድሃውም ሃብታሙም ከዘመድ አዝማድ ጋር በዚያች ትንሽ ወረቀት ይገናኝ ነበር። ታዲያ ተጽፋ ወደተፈለገችበት እስክትደርስ
ድረስ አንዳንድ ጊዜ እስከ አንድ ወርም ትወስድ ነበር። በአብዛኛው የኢትዮጵያ ከተሞችና መንደሮች ስልክ ስላልነበር፣ አቅሙ ያለው
ሰው እሷን ሊቀድማት የሚችለው ገንዘብ ከፍሎ በአውቶቡስ ተሳፍሮ በመሄድ ብቻ ነበር። እነ ቴሌክስና ቴሌግራም የሚባሉት ቴክኖሎጂዎች
ዋጋቸው ውድ ስለነበር ስራ ላይ የሚውሉት ብዙ ገንዘብ ባላቸው ድርጅቶችና መንግስታት ለዚያውም አስቸኳይና አጭር የሆኑ መረጃዎችን
ለመለዋወጥ ብቻ ነበር።
የዛሬ ሃያ አምስት ዓመት
ገደማ ደግሞ ቴለክስና ቴሌግራም ኋላ ቀር ሆኑና ዘመናዊውና ፈጣኑ መሳሪያ ፋክስ (FAX) የሚባለው ሆነ። በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1990ዎቹ
አጋማሽ ላይ ጀምሮ እንደ ሰደድ እሳት በምድር ሁሉ መያያዝ የጀመረው የዓለም አቀፉ የግንኙነት መረብ (ኢንተርኔት) ሲመጣ ደግሞ
እነ ቴሌክስ፣ ቴሌግራም፣ ፋክስና የቤት ስልክ ሳይወዱ በግድ መንገዳቸውን ወደ ሙዚየም ማቅናት ጀመሩ። ዘመናዊዎቹ ኢሜይልና ተንቀሳቃሽ
ስልኮች,በመገናኛ አደባባይ ላይ ባለዘመኖች መሆን ጀመሩ። ባለፉት አስር በማይሞሉ ዓመታት ደግሞ እነ ኢሜይልም ከሳሎን ቤት ወደ
ጓዳ ተገፉና፣ “መልእክት አሁኑኑ” (INSTANT
MESSAGING) የሚባለው የመገናኛ ዘዴ በተለይም ደግሞ በቀላሉ በኪስ በሚገቡ በብልጦቹ ስልኮች (SMART PHONES) አማካይነት
ሩጫውን ያሸነፈ ይመስላል። ይህም አልበቃ ስላለ ታዲያ እንደነ GOOGLE፣ MICROSOFT እና APPLE የመሳሰሉ ድርጅቶች ችግሩ
የሰው ልጅ ራሱ ቀርፋፋ ስለሆነ ነውና የሰውን ጭንቅላት ራሱን ከኮምፒውተር ጋር በማገናኘት የተሻሻለ ፍጥረት መስራት አለብን ብለው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብን በማፍሰስ የሰውን ልጅ ራሱን ኋላ ቀር
የሚያደርግ የሰውና የኮምፒውተር ዲቃላ ለመፍጠር ሌሊትና ቀን እየሰሩ ነው፤ ብዙ ርምጃዎችንም አድርገዋል። ይህ ጥረታቸውም በመንግስታት
በጀትም ሳይቀር ይደገፋል። ታዲያ ይኼ የሚያመራው ወዴት ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስስ ስለዚህ ምን ይላል? ጌታ እግዚአብሔር ሳያውቀው
የሚሆን አንድም ነገር የለምና በርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻው ዘመን እውቀት እጅግ እንደሚበዛና ሰዎችም ከስፍራ ወደ ስፍራ እንደሚራወጡ
ይናገራል። ለምሳሌ ዳንኤል 12 ቁጥር 4ን ተመልከቱ። ጌታ ቢፈቅድ የዚህን ነገር የወደፊት አቅጣጫና የመጨረሻ ውጤት ወደፊት በሚወጡ
አጫጭር መልእክቶችና በመለከት ድምጽ መጽሔትም ላይ እንነጋገርባቸዋለን።
ከላይ እንደተመለከትነው
ዛሬ በሰው ዘር ታሪክ ያልነበሩ እጅግ ፈጣንና ለመጠቀም ብዙም የማያስቸግሩ የመነጋገሪያና የመረጃ መለዋወጫ ዘዴዎች አሉን። እነዚህ
ሁሉ ግን በሰው ልጆች መካከል ያለውን የልብና ያለመግባባት ችግር ሊፈቱ አልቻሉም። መነጋገሪያው ፈጣን መሆኑ ክፋት ባይኖረውም፤
ችግሩ ያለው አሁንም የሰው ልብ ጋ ስለሆነ ቴክኖሎጂ እንደ ድምጽ ማጉሊያ የሰውን ልብ ጫጫታ በፍጥነትና በቀነሰ ዋጋ ያጓጉዘዋል
እንጂ ጫጫታውን መልክ ወዳለው ንግግር አይለውጠውም ወይም ለያንዳንዱ የሰው ልብ ጩኸት መልስ ሊሆን አልቻለም፣ አይችልምም። ይህን
ያልተረዳ የሰው ልጅ ግን ዛሬም ቢሆን ችግሩ የስልኩ፣ የኢንተርኔቱና
የቴክስቱ መንቀርፈፍ ነው ብሎ ያጉረመርማል።
ታዲያ በክርስቶስ ዳግመኛ
የተወለድን ክርስቲያኖችስ ዛሬ የምናሳድደው ምን ይሆን። አዳኛችንና ጌታችን የሰጠንን ወንጌልን ለሌሎች የማድረስ አደራና ትዕዛዝ
ለመወጣት ምን ያህል እንቸኩላለን፣ እንተጋለን? በደሙ ኃጢዓታችንን ካነጻ በኋላ ወደ ሰማይ የሄደውንና ተመልሼ እመጣለሁ ያለንን
ጌታ መጠበቁንስ ምን አድርገነው ይሆን? ጌታ ራሱ፣ ነቢያትና ሃዋርያትም እንዳስተማሩት ይህ ጌታ ባላሰብነው ሰዓትና ጊዜ ተመልሶ
ይመጣል። በሰማይ ደመና፣ በመላእክትና በቅዱሳን ታጅቦ በክብር ይገለጣል። ሊሞላ የማይችለውን ስጋዊና ምድራዊ ነገር ብቻ ወደው ጌታን
የገፉትና እምቢ ያሉት የምድር ወገኖች ሁሉ ጌታ በድንገት ሲገለጥ ዋይ ዋይ ይላሉ። (ራዕይ 1:6) ወንጌልን ያመንን እኛ ግን የጌታ ቀን እንደ ሌባ ይደርስብን ዘንድ በጨለማ አይደለንም።(1ኛ ተሰሎንቄ 5:4) የእግዚአብሔርን ቃል በልባችን እየሞላን፣
ለመንፈስ ቅዱስ ድምጽም ደግሞ ልባችንን ሳናደነድን በጌታ ያገኘነውን የህይወት ብርሃን እያበራን፣ በዚህ አለም ኮተታ ኮተት ልባችን
ሳይያዝብን ተግተን ሙሽራውን ኢየሱስን ልንጠብቀው ይገባል። እሱ ለሙሽራይቱ ቤተ ክርስቲያን ስፍራን ሊያዘጋጅ ሄዷል። እኛ የሙሽራይቱ
አካላት የሆንን ደግሞ የግል ህይወታችንም ሆነ ቤተ ክርስቲያን ሙሽራው በሚገለጥበት ጊዜ ያለውርና ያለነቀፋ ሆነው እንዲገኙ ተዘጋጅተን
እንድንጠብቀው ታዘናል። ስለዚህ ጌታችን በመጣ ጊዜ መብራታችን እንደበራና ወገባችንም እንደታጠቀ ሆነን በሩን ሲያንኳኳ ልንከፍትለት
እንዘጋጅ። “ይህን የሚመሰክር አዎን በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን
ጌታ ኢየሱስ ሆይ ቶሎ ና።” ራዕይ 22:20 አዘጋጅና አቅራቢ: ዶ/ር
በፈቃዱ አድማሱ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ