ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ ወደ ጦርነት መውጣት

ከእግዚአብሔር ጋር አብሮ ወደ ጦርነት መውጣት
በሚገፋችሁ ጠላት ላይ በምድራችሁ ወደ ሰልፍ (ጦርነት) ስትወጡ ከፍ ባለ ድምጽ መለከቶቹን ንፉ፣ በእግዚአብሔርም በአምላካችሁ ዘንድ ትታሰባላችሁ፣ ከጠላቶቻችሁም ትድናላችሁ። (ዘሆልቁ 10፤9)
የእግዚአብሔር ህዝብ እስራኤል ወደ ጦርነት እንዲወጡ ጌታ ይፈቅድላቸው ወይም ያዝዛቸው የነበረው በሁለት ምክንያቶች ብቻ ነበር። የመጀመሪያው ምክንያት እርሱ እንዲወርሱት የሰጣቸውን ምድር ለመውረስ ወደ ከነዓን ምድር በሚገቡበት ጊዜ የግድ በዚያ የነበሩትን ዓመጸኛ እና በአጋንንታዊ ሥርዓት ስር ይኖሩና የሰይጣን ተባባሪ የሆኑትን ህዝቦች ለማጥፋት ነበር። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እስራኤል ወደ ተስፋው ምድር ሲሄዱ በመንገድ ላይ ሊያጠቋቸው ከተነሱ እንደ አማሌቃውያን ካሉ ህዝቦች ወይም ደግሞ የተስፋውን ምድር ከወረሱ በኋላ ሊያጠፉአቸው ወይም ሊዘርፏቸውና ባሪያ ሊያደርጓቸው ከሚመጡ እንደ ፍልስጥኤማውያን፣ ሶርያውያንና ምድያማውያን ካሉ ጠላቶቻቸው ራሳቸውን ለመከላከል ነበር። አንዳንድ ጊዜ ግን የተለያዩ የእስራኤል መሪዎች ትክክል ያልሆኑ ጦርነቶች በራሳቸው ፈቃድ እያስነሱ ይዋጉ ነበር። ብዙውን ጊዜም እነዚህ ጦርነቶች የሚያመጡት ውጤት እልቂትና ጥፋት እንዲሁም ሽንፈት ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን (በዚህ በኛ ዘመን) የእግዚአብሔር ህዝብ ደግሞ ክርስቲያኖችና ናቸው። የክርስቲያን ጦርነት ደግሞ መንፈሳዊ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። በምድር ላይ የምናያቸውው በአገሮች፣ በህዝቦችና በግለሰቦችም መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችና ጦርነቶች ሁሉ ዋነኛው መንስኤዎቻቸው የሰው ልጅ ኃጢዓትና አለመታዘዝ እንዲሁም ደግሞ የሰውን ዘር ለማጥፋትና ለማመሰቃቀል ሌትና ቀን ተግተው የሚሰሩ የዚህ የጨለማው ዓለም መንፈሳዊ ገዢዎች የሚያደርጉት ትግል ነው።
በብሉይ ኪዳን በእስራኤልና በእስራኤል ጠላቶች መካከል የተካሄዱት ጦርነቶች በአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ከጨለማው መንፈሳዊ ዓለም ኃይላት ጋር ለሚያካሂዱት ጦርነት እንደ ጥላና ምሳሌ ናቸው። እግዚአብሔር አምላክ ህዝቡን ወደ ጦርነት ውጡ ብሎ በሙሴ፣ በኢያሱ፣ በዳዊት፣ በጌዴዎን ወይም በሌሎች መሪዎች በኩል ትዕዛዝና መመሪያ በሰጠበት ጊዜ፣ ህዝቡና መሪዎቹ ደግሞ የጌታን ትእዛዝ በትክክል ከተከተሉ ጦርነቱ ሁል ጊዜ የሚደመደመው በድል ነበር። ጌታ እግዚአብሔር ራሱ ሰላምና የሰላምም አምላክ ነው። ሞትን፣ ጦርነትንን እልቁትን ወደዚህ ዓለም ያስገባው ግን በትዕቢት ተነፍቶ ጌታ አምላክን እተካለሁ ብሎ ተነስቶ የነበረው ዲያብሎስ፣ ሰይጣን፣ ዘንዶና የቀደመው እባብ ተብሎ በተላያዩ ስሞች በመጽሐፍ ቅዱስ የሚጠራው ሉሲፈር የሚባለውና ከክብሩ የተጣለው ኪሩብ ነው። በዚሁ በሰይጣን ተታልሎ ክብሩንና ህይወቱን በውሸት የለወጠው የሰው ልጅም በዚህ የእልቂት አገንዳ ውስጥ ተባባሪ ሆኖ ይሰራል። የእውነተኛ ክርስቲያን ጦርነት ግን ይህንን ሰይጣን የሚያካሂደውን የፍጅትና የእልቂት አጀንዳ ለመመከትና ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ከዘላለማዊ ሞት እንዲያመልጡ ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ህዝቦች በሰላም መኖር ሲችሉና የክርስቶስ ወንጌልም የሚሰበክበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ደዘመዛሙርቱን ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፣ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ ብሎ ሲልካቸው፣ እርሱ ራሱም ደግሞ ከነሱጋር ሁልጊዜ እንደሚሆን ቃል ገብቶአል።

ስለዚህ በዚህ ዘመን የንጉስ ካህናት፣ ቅዱስ ህዝብና ለርስቱ የተለየ ወገን አድርጎ እግዚአብሔር የጠራን ክርስቲያኖች ሁሉ አምላካችን ላሰለፈን መንፈሳዊ ጦርነት ታጥቀን ልንነሳ ያስፈልጋል። ምድር በኃጢዓት ማጥ ውስጥ እየሰጠመች ነው። በምድር ሁሉ የንጹኃን ዜጎችና ደም በተለያዩ ጦርነቶች እንደ ደም እየፈሰሰ ነው። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ህጻናት የገቡበት ሳይታወቅ ይጠፋሉ። በቅርቡ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከነዚህ ህጻናት ብዙዎቹ በክፉ ሰዎች ርኩስ ወሲባዊ ጥቅም ይደፈራሉ፣ ይገደላሉ ለአጋንንትም እንደ መስዋዕት ይቀርባሉ። ይህ ደግሞ የሚካሄደው ድሃና ያላደጉ በሚባሉ በአፍሪካ፣ በደቡብ አሜሪካና በእስያ ብቻ ሳይሆን ሰልጥነናል፣ በልጽገናል በሚሉት አገሮችም ነው። እኛ  ክርስቲያኖች እነዚህን እኩይ ተግባራት በያለንበት አገርና ከተማዎች የመዋጋት ኃላፊነት አለብን። የህዝብን ደህንነት ከሚጠብቁ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ጋር በመልካም ስራ መተባበር ግዴታችን ነው። ከዚህ በላይ ግን የችግሩ መንስኤ መንፈሳዊ ነውና፣ ይህንን ክፋት የሚያቅዱትንና የሚያስፈጽሙትን የጨለማውን ዓለም መንፈሳዊ ኃይላት ከአምላካችን ጋር ወደ ጽድቅ ጦርነት በመግባት መዋጋት አለብን። ታዲያ ወደዚህ ጦርነት ለመግባትና ድል ለማድረግ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ሰራዊት መቀደስ አለብን። በዘሆልቁ ምእራፍ 10 ላይ ጌታ አምላክ እንዳዘዘው የጦርነትን መለከት የሚነፉት ካህናት ናቸው። ካህናት ደግሞ ለእግዚአብሔር የተቀደሱ፣ የተመረጡ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ጠንቅቀው የሚያውቁና በእግዚአብሔር ሥርዓት የሚሄዱ ሰዎች ናቸው። ወታደር ወደ ጦርነት ሲወጣ ብዙ ኮተታ ኮተት ተሸክሞ አይሄድም። መንፈሱን፣ አእምሮውንና ሰውነቱን ለጦርነት ያዘጋጃል። የመዋጊያ መሳሪያዎቹን ይይዛል። አብረውት የሚዋጉትን ሰዎች በሚገባ ይተዋወቃል። በጦር ሜዳ ላይም የሚግባቡባቸውና ለመረዳዳት የሚያስችሉአቸውን ቋንቋ ይማራሉ። ከአስር አለቃ ጀምሮ እስከ ጀነራል ድረስ መሪዎቻቸውን በሚገባ ያውቃሉ። ሁሉም ጠብመንጃ ይዘው ተኳሽ ብቻም አይደሉም። አንዳንዱ ስንቅ ያዘጋጃል፣ አንዳንዱ ያቀብላል፣ አንዳንዱ የቆሰሉትን ያክማል፣ ሌላው የደከሙትን ያበረታታል ወዘተ። ታዲያ በመንፈሳዊ ጦርነት የምንሳተፍ ክርስቲያኖችም ከዚህ ባላነሰ መዘጋጀትና መሰማራት ያስፈልገናል። ያንተ፣ ያንቺ ድርሻ ምንድ ነው? ያለ ጥርጥር ጌታ የጨለማውን ኃይል በመጋፈጥ የወንጌልን ብርሃን ጌታን ላላወቁት እንድናደርስ አዝዞናል። መለከት ተነፍቷል። አምላካችን በፊታችን ወጥቷል። ከታዘዝን፣ ለሱ ከተገዛንና በጽድቅ ከተዋጋን ድል ማድረጋችን የተረጋገጠ ነው። ንጉሳችንን ተከትለን በምስጋና፣ በዝማሬ፣ በጽድቅ፣ በቅድስና፣ በእውነት፣በትጋት፣ በፍቅር፣ በርህራሬና በትህትና እንውጣ። እንጸልይ። ቃሉን እናንብብና እናጥና። የወደቁትን እናንሳ፤ ተስፋ ያጡትን አይዞአችሁ እንበላቸው፣ የተበተኑትን እንሰብስብ፣ ጌታ ቀብቶ የላከልንን መሪዎች በትክክል እንለይና እንከተላቸው፤ ፍቅራችን በእውነትና በተግባር እንጂ ከንፈርን በመምጠጥና በማስመሰል አይሁን። የመለከቱን ድምጽ እንስማ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...