ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ በበረት ውስጥ የተኛ ህጻን አይደለም

ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ በበረት ውስጥ የተኛ ህጻን አይደለም፣ ነፍሳችንን ለዘላለም ለማዳን የሚጠራን የፍቅር ንጉስ እንጂ
በዚህ ምድር ከምንለማመዳቸው ዘላቂ ደስታዎች ሁሉ ልዩ የሆነው የአዲስ ልጅ መወለድ ነው የሚለውን አባባል ብዙ ሰው ይስማማበታል። ደስታዎች ብለን የምንጠራቸው ሌሎች ነገሮች ሁሉ ከዚህ ዋነኛ ደስታ የሚመነጩ ናቸው ብንልም፣ ሃሳቡ የፍልስፍና ይምሰል እንጂ እውነት መሆኑ የግድ ነው። ምክንያቱም እኛ ሁላችንም ደስታን የምንለማመደው በመጀመሪያ ወደዚህ ደስታውን ወደምንለማመድበት ዓለም የመጣነው በልደት ስለሆነ ነው። ወቅቱ ስለሆነ እያከበርነው ያለነውን የጌታን ልደትም (CHRISTMAS) ከዚሁ የአዲስ ሰው ወደዚህ ዓለም መምጣት ጋር እጅግ የተቀራረበ አድርገን እንድንገምት ያደርገናል። በርግጥም የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ለሰው ልጆች ሁሉ ታላቅ ወንድም፣ አዳኝና ጌታ የሆነው ፍጹም ሰውና ፍጹም አምላክ መምጣት ነውና ታላቅ ደስታ ልንደሰት ይገባል። በክርስቶስ ልደት  ምክንያት ያገኘነው ደስታ ደግሞ ከሰባ፣ ከሰማንያ ወይም ከዘጠና ዓመት በኋላ በሃዘንና በእንባ ወደመቃብር በምንሸኘው በኛ በሟች የሰው ልጆች መወለድ ከምናገኘው ደስታ እጅግ የላቀና ዘላለማዊ ነው። ይህን እውነት ከተገነዘብን ታዲያ ደስታችንም እንዲሁ ዘላለማዊ ነው ማለት ነው።
ይህንን የገናን እና የፈረንጆቹን አዲስ አመት ፌሽታ ረስተን ወደተለመደውና ወደ ግራና ወደ ቀኝ እንደሸማኔ መወርወሪያ ወደሚወዘውዘን ኑሮአችን ከመመለሳችን በፊት ልንገነዘብ የሚገቡን ትልልቅና ዘላለማዊ ቁም ነገሮች አሉ። ከነዚህም አንዱና ዋነኛው ይህ ልደቱን ያሰብነውና ያከበርነው ልዩ ሰውና የእግዚአብሔር ልጅ ወልድ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በዚህ ሰሞን እንደምናስበው አሁንም በቤተልሔም በረት ውስጥ በጨርቅ ተጠቅልሎ እረኞች ሊያዩት የሜመጡ ህጻን አይደለም። የዚህን የመሲሁን መምጣት በተመለከተ ትንቢትን ከተናገሩት ነቢያት አንዱ ነቢዩ ኢሳይያስ የዚያን፣ የዛሬ 2016 ዓመት ገደማ እንዲህ ብሏል፤
“ሕጻን ተወልዶልናል፣ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፣ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ በፍርድና በጽድቅ ያጸናውና ይደግፈው ዘንድ በዳዊት ዙፋንና በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፥ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።” ኢሳይያስ 9፤6፥7
የመወለዱን የምስራች ካበሰረ በኋላ፣ ነቢዩ ወዲያውኑ ስለዚህ ህጻን የገለጸው አንዱ ቁም ነገር “አለቅነት” ሁሉ ወይም በዛሬው ዘመናዊ አማርኛ “የመንግስት የበላይ ገዢነት” ሥልጣን በሱ ትከሻ ላይ እንደሆነ ነው። መሲሁን ይጠብቁ የነበሩ ብዙዎቹ የእስራኤል ሕዝብ ይህንን “ገዢነት” ወይም “አለቅነት” የተረዱት በመካከለኛው ምስራቅ በምትገኘው አገራቸው ታሪክና ከነበሩበት የፖለቲካ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ብቻ ነበር። የተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ በርግጥም በዳዊት ዙፋን ላይ ሆኖ በቃል ኪዳን የእግዚአብሔር ህዝብ በሆነው በእስራኤል ላይ የሚገዛ ቢሆንም፣ የመንግሥቱ ሥልጣን ግን በአንዲት አገር፣ አህጉር ወይም በምድርም ብቻ የተወሰነ አይደለም። መንግስቱ በዚህች በኛ ምድርና በላይዋ ባሉት አገሮችና፣ ድርጅቶች ሁሉ ላይ፣ ከዚያም አልፎ በሰማይና እኛ ሰብዓዊ ፍጡሮች በውስን ችሎታችን ልናውቃቸውና ልንደርስባቸው በማንችለው በቁሳዊና መንፈሳዊ ዓለማት ባሉ ፍጥረታትም ሁሉ ላይ ትገዛለች። በዚህ በምድራችን ላይ ለዘላለም ሊገዛ ያለው የክርስቶስ መንግስት ደግሞ እኛ የሰው ልጆች እንደምንመሰርታቸው በታሪክ እንዳለፉት፣ ዛሬ እንዳሉት ወይም ነገ ሊኖሩ እንደሚችሉት በፖለቲካ ሽኩቻ፣ በጦርነትና በተንኮል፣ በገንዘብ ብርታትና በማህበረሰባዊ ግፊት የሚመሰረት ወይም የሚጸና  አይደለም።
የክርስቶስ መንግስት ፍጹም ፍትህ፣ ጽድቅ፣ ሰላምና ፍቅር የሰፈነበት፣ ለስልጣንና ንብረት ክፍፍል ድርድር የማያስፈልግበት፣ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስና ወህኒ የማያሻው፣ የአማካሪዎች ጉባኤና ምርጫ፣ ሰይፍና ጦር የሚረሱበት፣ በዘመንና በቦታ የማይወሰን ዘላለማዊ መንግሥት ነው። ይህን መንግሥት እውን ለማድረግ ደግሞ የዚህ መንግሥት ራስና ቁንጮ የሆነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እያንዳንዱን የመንግስቱን ዜጋ የሚመርጠው ኑ ገንዘብ አዋጡልኝ፣ ደግፉኝ በማለት ሳይሆን የኃጢዓታቸንን እዳ ራሱ በመስቀል ላይ ሞቶ ከከፈለና የምንወርሰውንም ግሩም ድንቅ ዓለም ራሱ ካዘጋጀ በኋላ ነው። ይህንን ጌታና አምላክ በቀጥታ ለማወቅ፣ ለማመንና ለመቀበል እድል የማይሰጠው የሰው ልጅ የለም። የመንግስቱ ዜግነትም የሚሰጠው ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋና ከብሔሮችም ሁሉ ለመጡ ለትልልቆችና ትንንሾች፣ ባለጸጋዎችና ድሆች፣ ለመኳንንትና ተራ ሰዎች፣ ለተማሩና ላልተማሩም፣ ለወንዶችና ሴቶችም ሁሉ ነው። በክርስቶስ የማመንና የዘላለማዊው መንግሥት ዜግነት እድል የሚገኘው ደግሞ ሞኝነት በሚመስለው በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መሰበክ የሚተላለፈውን የእግዚአብሔርን ቃል በማመን ነው።
የኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌል መልእክት ሰማያዊና ዘላለማዊ ስለሆነ፣ እኛ ምድራውያን የሆንን ሰዎች ባሉን አምስት የስሜት ህዋሳት፣ በአእምሮ ችሎታችን፣ በእውቀታችን፣ በልምዳችንና ነገሮችን በማገናዘቢያ ተሰጥዎዎቻችን ብቻ ልረዳው አንችልም። የወንጌልን ሰማያዊ መልዕክት ሊሰማና ሊረዳ የሚችለው መንፈሳዊ ማንነታችን በኃጢዓት ምክንያት ሞቷልና። ውስጣዊው ማንነታችን (ነፍሳችን፣ ህሊናችን) ግን በጥልቅ ሊረካ በማይችል ጥማት ይሰቃያል። ብዙዎቻችን ታዲያ የነፍሳችንን ጥያቄና ጥማት አፍነን የራሳችንን ክብርና የሰውን ምስጋና ከመፈለግ የተነሳ የሰው ወግ የሰጠንን የከንቱ ውዳሴ ካባ ለብሰን ደስተኞች መስለን እንኖራለን። በዚያ በሚሞቀው ካባችን ውስጥ ሆነንም ታዲያ ነፍሳችን ወደፈጣሪዋ መጮኋን አታቋርጥም። ይኼ የገናው ህጻን ኢየሱስ ክርስቶስም ያንን የነፍሳችንን ጩኸት ይሰማል። ለያንዳንዳችን በግላችን፣ ለሰው ልጆች ሁሉም በጋራ የዛሬም ሆነ የነገ መልስ አልባ ጥያቄዎቻችን መልስ ያለው በዚህ አስደናቂ ሰውና አምላክ በኢየስስ ክርስቶስ እጅ ነው።

ክርስቶስ ዛሬ የሚጠራን ቤተልሔም ከተማ ባለች አንዲት የማረፊያ ሆቴል በከብቶች በረት ውስጥ ህጻን ሆኖ ተኝቶ ስጦታዎችን እንድናመጣለት ሳይሆን፣ በቀራንዮ መስቀል ላይ ስለኛ ሞቶ፣ የሞትን ኃይል ድል አድርጎ፣ በክብር እስኪመለስና ዘላለማዊ መንግስቱን እስኪመሰርት እንዲሁም እኛ ሁላችንም ንስሐ እስክንገባ ድረስ በትዕግስት ከሚጠብቅበት ከእግዚአብሔር አብ ዙፋን ቀኝ ሆኖ እንድናምነውና ከዘላለም ሞት እንድናመልጥ ነው። ለመንግሥቱ መገለጥም ቀንን ቀጥሮአል፣ እኛ መቼ መሆኑን አንወቅ እንጂ። ስለዚህ የገና ደስታችንን ድምቀቱ በቀኖች ማለፍና በኑሮ ውጣ ውረድ እየፈዘዘ ከመሄዱ በፊት የዚህን የገናውን ጌታ ጥሪ እንስማ። ክርስቶስን ያላወቅነው ሁሉ ንስሃ ገብተን ዛሬ እንቀበለው። የምናምነውና ነፍሳችንን አደራ የሰጠነው አማኞች ደግሞ በተሰጠን የዘላለማዊ ሰላም፣ የደስታና የተስፋ ኃይል በመበርታት የወንጌሉን የምስራች ላልሰሙ ሁሉ እንንገር። ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ በበረት ውስጥ የተኛ ህጻን ሳይሆን፣ በክብር ተገልጦ የዘለዓለም መንግስቱን በፍጥረት ሁሉ ላይ ለመመስረት የሚጠብቅ የምድር ገዢዎች ሁሉ የበላይ ጌታ፣የመንፈሳዊውና የቁስ አካላዊውም ዓለም ሁሉ መስራችና ዘላለማዊ ባለቤት ነው። አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...