ከሁሉም የላቀ የአዲስ ዓመት ውሳኔ ፥ የሕይወትን እንጀራ መብላት፣
የሕይወትን ውኃ መጠጣት
ከምዕራቡ ዓለም የአዲስ
ዓመት አከባበር ወጎችና ልማዶች አንዱ እያንዳንዱ ሰው በአዲሱ ዓመት ይህን ወይም ያንን ማድረግ አለብኝ ወይም ማድረግ እፈልጋለሁ
ማለትና ጥቂት ነገሮች በመምረጥ ከራሱ ጋር ቃል መግባት ነው። አንዳንዱ ሰው ጤናውን ለማሻሻል የአካል እንቅስቃሴን መጀመር ሲሻ፣
ሌላው ኑሮውን ለማሸነፍ የተሻለ ሥራን ለመያዝ ያቅዳል፣ አንዱ የተሻለ ትምህርትን ለመጀመር ሲያስብ፣ ሌላው ደግሞ ትዳር ለመመስረት ይነሳል። ልጅ የሌላቸው ልጅ ለመውለድ ሲዘጋጁ፣ ልጆች ያሏቸው
ደግሞ ልጆቻቸውን በተሻለ መንገድ ለማሳደግ ቃል ይገባሉ። ሌሎች ደግሞ
ሌሎች እቅዶችን ያቅዳሉ፣ ይፈልጋሉ ውሳኔንም ያደርጋሉ።
እቅድ መልካም፣ ውሳኔም
ጥሩ ነው። ታዲያ የሚፈልጉትን ሁሉ ማድረግ አስቸጋሪ ወይም ከባድ ነውና፣ ውሳኔዎችን ቅደም ተከተል በማስያዝ አንዱ ወይም ሁለቱ
ላይ ማተኮር እጅግ ይጠቅማል። ከውሳኔዎች ሁሉ በላይ የሚበልጥ ውሳኔ፣ ከምርጫዎችም በላይ የሚበልጥ ምርጫ ደግሞ አለ። በመጀመሪያ እረኛ የነበረና የወንድሞቹ ሁሉ ታናሽ ወንድም ቢሆንም የኋላ ኋላ የእስራኤል ንጉስና የእግዚአብሔር የልብ ሰው
የተባለለት ዳዊት ገና በልጅነቱ ነበር ከምርጫዎች ሁሉ በላይ የሆነውን ምርጫ የመረጠው። ሌሎች ፍላጎቶቹንም ለዚህ ለዋነኛው ምርጫው
የበታች አድርጎ አስቀመጣቸው። ያንን ታላቁን ምርጫውን እንዲህ ሲል ነው ዳዊት የገለጠው፤
“እግዚአብሔርን
አንዲት ነገር ለመንሁት እርስዋንም እሻለሁ፤ በህይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም
አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ።” መዝሙር 27፥4
ዳዊት አምላኩን ለማወቅ፥
ወደሱም ተጠግቶና እሱን ደስ እያሰኘ ለመኖር የነበረው መሻትና ውሳኔ እጅግ ጠንካራ ስለነበር ይህ ፍላጎቱን በረሃብና በጥማት መልክ
ይገልጠው ነበር። በመዝሙር ምዕራፍ 42 ላይ ለምሳሌ እንዲህ ይላል፤
“ዋላ ወደ
ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ አቤቱ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች።
ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፣ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ?” መዝሙር 42፤1ና2
በዚህም ሕይወት ሆነ በሚመጣው
ዓለም እግዚአብሔርን እንደማወቅና ወደርሱም ተጠግቶ በፍቅሩ ሥር እንደመኖር አስደናቂ፣ አስደሳች፣ አርኪና፣ ዘላቂ ነገር የለም።
በአዲሱ ዓመት ካወጣናቸው እቅዶችና ውሳኔዎች ሁሉ ዋነኛው እግዚአብሔርን ማወቅ፣ በበለጠ ወደርሱ መጠጋት እና እግዚአብሔርም በጌታ
በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለኛ የገለጠውን ፍቅር መለማመድ፣ እሱን መታዘዝና በረከቱንም ለመቀበል መዘጋጀት ዋነኛዎቹ ካልሆኑ ሌሎቹ
ምርጫዎቻችን ትክክለኛውን ቅደም ተከተል አልያዙም። የምናገኘውን ነገር ሁሉ አንድ ቀን ጥለነው እንሄዳለን። እግዚአብሔርን ችላ ብለን
የምንሰበስበው ሁሉ የግድ አንድ ቀን ይበተናል። የምርጫችን ሁሉ ቁንጮ፣ የጥማታችንና የመሻታችን ሁሉ ዋነኛው ትኩረት ጌታ እግዚአብሔር
ከሆነ ግን በዚህች አጭር ሕይወትም ሆነ በሚመጣው ዘለዓለም እጅግ የተደሰትን፣ ሙሉ ሰላም ያለንና የተባረክን ሰዎች እንሆናለን።
እውነተኛው የሕይወት እንጀራ፣
የሚያረካው የሕይወት ውኃ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህንን እንጀራ መብላትና፣ ከዚህም ውኃ መጠጣት ከአዲሱ ዓመት ውሳኔዎቻችን
ሁሉ ዋነኛው ቢሆን ለዘላለም አትራፊ እንጂ የከሰርን አንሆንም። ይህ ጌታ ደግሞ እኛ ከምንፈልገው ይልቅ ፈልጎን እኛ አለንበት ድረስ
መጥቷል ዛሬም ይመጣል። ባለንበት የእድሜ፣ የእውቀት፣ የኢኮኖሚ፣ የጉልበት፣ የጤና ሁኔታና ደረጃ ሊያገኘን ይናፍቃል። ይህች ቀን
በምድር ላይ የቀረን እድሜአችን የመጀመሪያይቱ ቀን ናት። ታዲያ በዚህች ቀን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል እንዲህ
ሲል ይጠራናል፤
“እናንተ
የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ፣ ብሉም፥ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። ገንዘብን
እንጀራ ላይደለ፣ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፣ በረከትንም ብሉ ሰውነታችሁ በጮማ ደስ ይበለው።
ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፣ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች፣ የታመነችውንም የዳዊትን ምሕረት፥ የዘላለምን ቃል
ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ። ” ኢሳይያስ 54፤1፥3
ክርስቲያንም ብንሆን ገና
ያላመንንን ሰዎች ጌታ እግዚአብሔር በሱ በኩል ሊደረግ የሚገባውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ወዳዘጋጀው የዘላለም ሕይወት ድግስ በክርስቶስ
ይጠራናል። በዛሬይቷም ቀን ሆነ በነዚህ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያው ቀናት ምርጫችን ወደሱ መቅረብ ከሆነ ሌላው ነገር ሁሉ ሳይወድ
በግድ ቦታውን ይይዛል። የያዘ ባይመስለንም ደግሞ በክርስቶስ ሆነን የዘላለሙን ሕይወታችንን ከያዝን ሌላውን ነገር ሁሉ በላቀና በከበረ
መንገድ ሳንፍጨረጨር ለዘለዓለም እናገኘዋለን።
ስለዚህ የዚህ የአዲሱ ዓመት
ዋነኛው ውሳኔያችን በልተነው እንደገና የማንራበውን የሕይወትን እንጀራ ለመብላት እና ጠጥተነው እንደገና የማንጠማውን የሕይወትን
ውኃ ለመጠጣት ይሁን። ይህ የሕይወት እንጀራና የሕይወት ውኃ ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፤
“ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፥ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም፥
በእኔ የሚያምንም ሁል ጊዜ ከቶ አይጠማም።” የዮሐንስ ወንጌል 6፥35
“መንፈሱና ሙሽራይቱም፤ ና ይላሉ። የሚሰማም፤ ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን
ውኃ እንዲያው (በነጻ፣ በጸጋ) ይውሰድ።” የዮሐንስ ራዕይ ምዕ 22 ቁ 17
አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር
በፈቃዱ አድማሱ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ