ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና፣ ማቴዎስ 24፤44 ትምሕርት ቁ 1 እና 2
መጽሐፍ ቅዱስን በጥሞና
የሚያነብና የሚያጠና እንዲሁም አምላኩንና ጌታውን የሚወድና ለመታዘዝ የሚተጋ ክርስቲያን ሁሉ ከምንም በላይ የሚናፍቀው ነገር ቢኖር
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ሲመለስና ይህንን እየተተራመሰ ያለውን ፍጥረተ ዓለም ከጥፋት ታድጎ በጽድቅና በእውነት ሲነግስ
ማየት ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ታላቁ ተስፋም ይኽው የጌታ ዳግም ምጽዓትና ለዘለዓለም መንገስ ነው። ታዲያ ክርስቲያን የሚናፍቀውን
ይኼንን የጌታን ዳግም ምጽዓት እጅግ የሚፈሩትና እንዳይመጣም የሚሹና ቢቻላቸውም ሊያስቀሩት የሚጥሩም አሉ። አንዳንዶቹም እነሱ ራሳቸው
ክርስቶስ ነን ይኸው መጣን በማለት ክርስቲያኖችን ለማሳሳት እንደሚሞክሩና ብዙዎችንም አሳስተው እንደሚወስዱ ጌታችን ራሱ በወንጌል
አስተምሮአል። ታዲያ መቼ ነው ጌታ የሚመለሰው፣ ቀኑ መቃረቡንስ እንዴት ነው የምናውቀው የሚለው ጥያቄ የኛ ብቻ ሳይሆን ከጌታ ጋር
በአካል በምድር ላይ አብረው የነበሩት የሐዋርያትም ያነሱት ነበር። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዳግም ምጽዓቱ በወንጌል ውስጥ ካስተማረባቸው
ብዙ ቦታዎች መካከል ትልልቆቹ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24፣ የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 13 እና የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ናቸው።
በነዚህ ሶስት ዋና ዋና በሚባሉ የዳግም ምጽዓቱ ትምህርቶች ውስጥ ደቀ መዛሙርቱ በሚገባ እንዲያስተውሉ ጌታ ያስተማረው ትምህርት
በሁለት አምድ በሚሆኑ መሰረታዊ ነገሮች ውስጥ ሚዛኑን የጠበቀ ነው ለማለት ይቻላል። የመጀመሪያው የእውነት አምድ ክርስቲያኖች ሁሉ
“እኔ ክርስቶስ ነኝ” ዘመኑ ቀርቦአልና ይኽው መጥቻለሁ ከሚሉ ሃሰተኛ ክርስቶሶችና ሃሰተኛ ነቢያት እንዲጠበቁ ጌታ ማስጠንቀቁ ነው።
ሁለተኛው አምድ ደግሞ ክርስቲያን ነኝ የሚል ሰው ሁሉ “ጌታ እስኪመጣ ይዘገያል” በሚል እንዝህላልነት፣ በዓለማዊነትና በስጋዊነት
ኑሮ ተዘፍቆ የጌታ ቀን በድንገት እንዳይመጣበት ማስገንዘቡ ነው። ስለዚህ የጌታን ዳግም ምጽዓት በተመለከተ እያንዳንዱ ክርስቲያን
በግሉም ሆነ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እንደ አንድ አካል በነዚህ በሁለቱ ሚዛን ጠባቂ የእውነት ዓምዶች መካከል በመቆም ታላቁን
የወንጌል ተስፋ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ዳግም ምጽዓት ማወጅ፣ ማስተማርና ለመምጣቱም ተዘጋጅተው መኖር አለባቸው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ
ከሞት ተነስቶ ካረገ ሁለት ሺህ ዓመት ሊሆን የቀረው ትንሽ ነው። የጌታ ሐዋርያት በምድር ላይ ከነበሩባቸው ከመጀመሪያው ምዕተ ዓመትና
ዓመታትና ከዚያም በሚቀጥሉት ብዙ ምዕተ ዓመታት የነበሩት ክርስቲያኖች በነሱ ዘመን ጌታ ይመለሳል ብለው ተስፋ በማድረግ ይኖሩ ነበር።
ይህንንም በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተጻፉት የሐዋርያት መልእክቶችና በቤተ ክርስቲያንም ረጅም ታሪክ ውስጥ ተጽፎ እናገኘዋለን። ታዲያ
ለምንድር ነው በዚህ እኛ ባለንበት በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች ስለ ጌታ ዳግም ምጽዓት ብዙም የማንማረው፣ የማንሰብከው?
ለዚህ ጥያቄ መልሱ በዚያው በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ አለ። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ሙሽራን በሚጠብቁ ሰዎች ምሳሌ በማድረግ በማቴዎስ
ምዕራፍ 25 ከቁጥር 1 እስከ 13 ድረስ ባስተማረው ትምህርት ላይ ዘመኑ እየረዘመ ሲሄድ ብዙ ክርስቲያኖች ጌታ ከመምጣት የዘገየ
መስሏቸው እንደሚዳከሙና፣ ሳያስቡት በድንገት ሲመጣም ብዙ ውካታ እንደሚሆን ገልጿል። በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ላይ ደግሞ የሱ
መምጣት በኖህ ዘመን የነበረውን ሁኔታ እንደሚመስል ጌታ በግልጽ አስተምሮአል። ስለዚህ የጌታ ዳግም ምጽዓት መድረሱን የምናውቅበት
አንዱ መንገድ በኖህ ዘመን የነበረውን ሁኔታ በሚገባ ማስተዋል ነው ማለት ነው። በሚቀጥሉት መልዕክቶቼ ላይ ይህንን በተመለከተ አጠር
አጠር ያሉ መረጃዎችን ከእግዚአብሔር ቃል፣ ከረጅሙ የቤተ ክርስቲያን ታሪክና እንዲሁም ደግሞ በትምህርቱና በምርምሩ ዓለም ካሉ ግኝቶችና
ተጨባጭ ማስረጃዎች በማገናዘብ አቀርባለሁ። የበለጠ ዝርዝር ትምህርቶችን ለማድረግ የምትፈልጉ ደግሞ በየወሩ የሚወጣውን የመለከት
ድምጽ መጽሔትን ተከታተሉ። በመጽሔቱ ላይም ለማቅረብ የሚረዝሙ ነገሮችን በተመለከተ ደግሞ ተጨማሪ ማስረጃ የሚሰጡ የመጽሐፍ ቅዱስ
ክፍሎችንና ሌሎች መጻህፍትን የሚያመላክት መረጃ በመጽሔቱ ላይ ይሰጣል። እስከዚያው ድረስ ግን በጸሎትና በጥሞና ከላይ የተጠቀሱትን
ስለዳግም ምጽዓቱ ጌታ ያስተማረባቸውን ክፍሎች አንብቡ። የጌታ መምጣት እጅግ በተቃረበበት ዘመን ውስጥ ነው የምንኖረው። ቃሉ በእጃችን
ሆኖ፣ የጌታ ቀን እንደ ሌባ ሊደርስብን አይገባም። ጌታ ራሱ እንዲህ ብሎናል፤
“ስለዚያች ቀንና ስለዚያች
ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም። የኖኅ ዘመን እንደነበረ የሰው ልጅ መምጣት
እንዲሁ ይሆናልና። በዚያች ወራት ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ፣ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደነበሩ፣ የጥፋት
ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከወሰደ ድረስ እንዳላወቁ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።” ማቴዎስ 24፤37
ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት
ኖኅ የሚባለው ጻድቅ ሰው በምድር ላይ በሚኖርበት ዘመን፣ እግዚአብሔር አምላክ፤ ከሱና ከሰባት ቤተሰቡ፥ እንዲሁም ደግሞ ተመርጠው
እሱ ወደ ሰራት መርከብ በመግባት ካመለጡት እንስሳት በስተቀር፤ የሰውን ዘርና እንስሳትን በሙሉ በውሃ እንዳጠፋ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል።
የጥፋት ውኃ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሃይማኖቶች፣
በአገሮችና ትውልዶች ታሪኮችም ውስጥ በስፋት የተዘገበና የሚነገር እውነታ ነው። የጥፋት ውኃ ምድርን ሁሉ አጥለቅልቆ ታላቅ ጥፋት
መፍጠሩ ዛሬ በአርኪዎሎጂ እና በሌሎችም ሳይንሳዊ የምርምር መስኮችም ጭምር ተረጋግጧል። የጥፋትን ውኃ ታሪክ በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ
6፣7፣ 8 እና 9 ላይ እናነባለን።
ለምንድ ነው እግዚአብሔር
የምድርን ሕዝብና እንስሳት ሁሉ በውኃ ለመደምሰስ የወሰነው የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ በተለምዶ የሚነገረንና የተማርነው ነገር ቢኖርበዚያን
ዘመን ኃጢዓት ስለበዛ ነው የሚል ብቻ ነው። እንደሌሎቹ ብዙዎች የብሉይ ኪዳን ክፍሎች ሁሉ ይህም ክፍል ጠለቅ ያለ መንፈሳዊ ትምህርት
አይሰጥበትም። ከኖህ ዘመን በኋላና እስከ ዛሬም ድረስ በምድር ላይ ከምናየው ኃጢዓት የበለጠ ምን ዓይነት ኃጢዓት ቢሰራ ነው ጌታ
ምድርን ፈጽሞ ለማጥፋት የሰወነው ብለን መጠየቅ ያሻል። መጽሐፍ ቅዱሳችንን ቀስ ብለን ካጠናንና በምድርም ሁሉ ላይ ያለውን መረጃና
እውቀቶች ከመረመርን ለዚህ ከባድ ጥያቄ መልሱን ብዙም ሳንደክም እናገኛለን። በርግጥም በኖህ ዘመን እጅግ የከፉ ኃጢዓቶች ተሰርው
ነበር። እነዚያ ኃጢዓቶች ግን እኛ በተለምዶ ኃጢዓት ብለን የምንላቸው ብቻ ሳይሆኑ መሰረታዊ የሆኑትን የጌታ አምላክን ሰማያዊና
ምድራዊ የፍጥረት ሥርዓቶች ሁሉ የጣሱና ፍጥረትን ለማጥፋት የታቀዱ ነበሩ።
በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖች
ስለ ኃጢዓት ያለን መረዳት ጠባብና በአብዛኛውም በአሰርቱ በሙሴ በተሰጡት ትዕዛዛት ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። ኃጢዓት ማለት በመሰረቱ
ዐመጽ ነው፣ በጌታ አምላክና በስርዓቱ ላይ ማመጽ። ኃጢዓት ማለት ጌታ አምላክ ፍጥረቱ እንዲከተለው የዘረጋውን ሥርዓት መቃወምና
ማፍረስ ነው። አሰርቱ የሙሴ ትዕዛዛት ኃጢዓትን በሙሉ አይገልጹም። የኃጢዓትን ምንነት ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ በሚገባ መረዳት
ያስፈልገናል። ለምሳሌ፣ የፍትህ መጓደልና ተገቢ ያልሆነ አድልዎ ጌታ አምላክን እጅግ የሚያስቆጣው በደል ነው። እንዲሁም ደግሞ ጌታ
እግዚአብሔር ምድርንና ሰማይን፣ በተለይም ደግሞ እንስሳትንና ተክሎችን ሁሉ በፈጠረ ጊዜ ፍጥረታትን በጾታና በዘር በዘራቸው ከፋፍሎ
ነው የፈጠራቸው። እያንዳንዱ እንስሳና ተክል የራሱን ፍሬ እንዲያፈራ በየዘሩ ወገን ውስጥ እንዲባዛ ጌታ አምላክ አዝዟል። በዘፍጥረት
1 ከቁጥር 11 እስከ 12 ድረስ ተክሎችን በየወገናቸው እንደ ፈጠረ እንማራለን። በዚሁ በዘፍጥረት 1 ከቁጥር 20 እስከ 22 ደግሞ
የአየር፣ የምድርና የባህር እንስሳትን ፈጥሮ እያንዳንዳቸው በየወገናቸው እንዲበዙና እንዲባዙ ትዕዛዝን ሰጠ። ይህም ማለት እያንዳንዱ
የተክልና የእስንሳ ዘር መባዛት ያለበት ጌታ በመደበለት በየወገኑ ውስጥ ብቻ ነው ማለት ነው።
በፍጥረት መጀመሪያ ላይ
ጌታ አምላክ የነበረው አላማ ይህ መሆኑን ደግሞ ከጥፋት ውኃ በኋላ ብዙ ቆይቶ በሙሴ በኩል በሰጠው ህግ እንዲህ ሲል አረጋግጧል፤
“ሥርዓቴን ጠብቁ። እንስሳህ
ከሌላ ዓይነት ጋር አይደባለቅ፥ በእርሻህም ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ፣ ከሁለት ዓይነት ነገር የተሰራ ልብስ አትልበስ።” ዘሌዋውያን
19:17 እና 18።
የሰው ልጆችም ደግሞ ለጾታቸውና
ለሰብዓዊነታቸው ተገቢ በሆነ ባህርይ ብቻ እንዲገዙ አዝዟል። ፍትወተ ሥጋን በተመለከተ ለምሳሌ ጌታ አምላክ ወንድ ከወንድ ጋር፣
ወይም ሴት ከሴት ጋር ፍትወተ ሥጋን እንዳይፈጽሙ፣ እንዲሁም ደግሞ አንድ ወንድ ወይም ሴት ከእንስሳ ጋር ፍትወተ ሥጋ እንዳይፈጸሙ
እንዲህ ሲል አዝዟል።
“ከሴትም ጋር እንደምትተኛ
ከወንድ ጋር አትተኛ፣ ጸያፍ ነገር ነውና። እንዳትረክስባትም ከእንስሳ ጋር አትተኛ፣ ሴት ከእርሱ ጋር ትተኛ ዘንድ በእንስሳ ፊት
አትቁም፥ የተጠላ ነገር ነውና።” ዘሌዋውያን 18፤22 እና 23።
ከእግዚአብሔር ሌላ አማልክት
የሚባሉትን ማምለክና ለዚህም አምልኮ ህጻናትን መስዋእት ማቅረብ እጅግ የከፋ ኃጢዓት መሆኑን በዚሁ በዘሌዋውያን 18 ላይ በማስተማር
ጌታ አምላክ የእስራኤል ልጆች ይህንን እና ከላይ የተጠቀሱትን ኃጢዓቶች ቢያደርጉ ምድሪቱ እንደምትተፋቸው እሱም እንደሚያጠፋቸው
አስጠንቅቋቸዋል።
በኖኅ ዘመን ምድርን ፈጽሞ
እስኪያጠፋ ድረስ ጌታ አምላክን ያስቆጣውን ዓመጽ የፈጸመው የሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን የሰማይ ልጆችም (በዘፍጥረት 6 ላይ የእግዚአብሔር
ልጆች የተባሉ ፍጥረታት) ነበሩ። ይህ ዓመጽ እጅግ የከፋና የፍጥረትን ምንነት በተለይም የሰውን ዘር ፈጽሞ ለማጥፋት
የተቃረበ ዓመጽ ነበር። አስተውለን ካነበብነው መጽሐፍ ቅዱስ የሆነውን ነገር በግልጽ ያስረዳናል። ስለዚህም የሚመሰክሩ ሌሎች እጅግ
ብዙ የታሪክ፣ የአርኪዎሎጂ፣ የህብረተሰብና የሌሎች ሃይማኖቶች መረጃዎችም አሉ። ለዚህ ለጥፋት ውኃ ፍርድ ዋነኛ መንስኤ ስለሆነው
የዓመጽ ሁሉ ዓመጽና ከዚያም ስለተከተሉት ነገሮች በዘፍጥረት ምዕራፍ 3 እና ምእራፍ 6 ላይ የተጻፉትን በቅርብ ማጥናት ያሻል።
ዘፍጥረት 6ን ከማጥናታችን በፊት ግን ከጥፋት ውኃ በፊት በምድር ሁሉ ተሰርተው የነበሩ እጅግ አስደናቂና አስገራሚ የሚባሉ፣ የሰው
ልጅ ዛሬም እንኳን ባለው የእውቀት ደረጃና ቴክኖሎጂ ሊሰራቸው የማይችሉ ብዙ ህንጻዎች፣ ሃውልቶች፣ ማዕከሎችና በምድር ሁሉ ያሉ
የጥንት ከተማዎችንና የኗሪዎቹን ቅሪቶች እንመለከታለን። ከነዚህም መካከል የግብጽ ፒራሚዶች፣ በሊባኖስ ባአልቢክ የሚገኘው የጁፒተር
ቤተ መቅደስ ቅሪት፣ በካምቦዲያ የሚገኘው የአንግ ኮር ዋት ቤተ መቅደስ ቅሪት፣ በሜክሲኮ፣ በፔሩ እና በሌሎችም የደቡብ አሜሪካ
አገሮች የሚገኙ እጅግ ብዙ ፒራሚዶች፣ ቤተ መቅደሶች፣ ታላላቅ የጥንት የአምልኮና የስፖርት ማእከሎች፣ ከተማን ከከተማ እና አገርን
ከአገር የሚያገናኙ የመሬት ውስጥ ዋሻዎችና መንገዶች እንዲሁም ባህር የከደናቸው ከተሞችና ቅሪቶች ይገኙበታል። እንዲሁም ደግሞ ቁመታቸው
ከ3 እስከ 6 ሜትርና ከዚያም በላይ የሆኑ ግዙፍ ሰዎችና ሰው መሰል ፍጥረቶች ዓጽሞችና ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቁሶችና ቅሪቶች በዓለም
ሁሉ መኖራቸው ተረጋግጧል። እነዚህ ሁሉ እርስ በርሳቸውም ሆነ በኖኀ ዘመን ከመጣው የጥፋት ውኃ ጋር፣ ከዚያም በበለጠ ደግሞ ከዚህ
ከኛ ዘመንና ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ጋር ያላቸውን ግንኙነቶች በተመለከተ የሚቀጥሉ ትምህርቶችን ከፈል ከፈል አድርጌ
አቀርባለሁ። እስከዚያ ድረስ ከላይ የተጠቀሱትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፣ በተለይም ደግሞ ዘፍጥረት ምእራፍ 1፣ ምእራፍ 6 እስከ
9፣ ዘሌዋውያን 18 እና 19ኝን አንብቡ። አዘጋጅና አቅራቢ፤ ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ