በኖኅ ዘመን ምን ሆነ? ትምህርት 4
ይህንን ትምህርት ለመረዳት የቀደሙትን ትምሕርቶች ማንበብ ያስፈልጋል። በትምህርት
3 መጨረሻ ላይ በጣም ባጭሩ እንዳቀረብሁት፣ በግብጽ የሚገኘውን ትልቁን የጊዛ ፒራሚድና ሌሎችንም በምድር ላይ ያሉ እጅግ አስገራሚና
ትልልቅ ስራዎች ማን ሰራቸው የሚለው ጥያቄ እስከ ዛሬ ድረስ ሳይንሳዊና ታሪካዊ ወይም በመረጃ የተደገፈ መልስ ያላገኘ ጉዳይ ነው።
ታዲያ ማን ሰራቸው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ታዲያ አንዳንዶች ከሌላ ዓለም የመጡ ፍጥረታት (ALIENS) ወይም የህዋ ተጓዦች የሚለውን
ሃሳብ ሲፈጥሩ ሌሎቹ ደግሞ ሊዋጡ የማይችሉ የፈጠራ መልሶችን በማቅረብ እንደኛው ያሉ በድንጋይና በነሃስ መሳሪያ ብቻ ይጠቀሙ የነበሩ
ሰዎች ናቸው የሰሩት በማለት ፍንክች አንልም ብለዋልል። እውነቱን ሊረዳ ለሚፈልግ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው
የሰው ዘርና ፍጥረት በሙሉ ላለበት ቀውስና መውጫ የሌለው ችግር ሙሉ መልሶች አሉት። እስቲ አሁን ደግሞ ታዲያ ወደዚህ ወደዘለዓለማዊው
የእውነት ኢንሳይክሎፒዲያ መለስ እንበልና የሚለውን እንመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የፈጠራቸውና ህይወት ያላቸው ፍጥረታት መላእክት (ወይም
ሰማያዊ፣ መንፈሳዊ ፍጡራን) የሰው ዘር፣ እንስሳትና እጽዋት ከዚያም
ደግሞ ርኩሳን መናፍስት ወይም አጋንንት ብቻ እንደሆኑ ያስተምራል። ታዲያ እነዚህ የዛሬው ዘመን አዋቂና ምሁራን እንዲሁም ተመራማሪዎች
ነን የሚሉት ALIENS ብለው የሚጠሩት ከነዚህ ፍጥረቶች የትኞቹን ነው። ከነዚያ ከዋክብት፣ ከነዚያ ፕላኔቶችች፣ ከዚያኛው ጋላክሲ
የመጡ ናቸው የሚለው ምናባዊ እውቀት ምንም መረጃ የሌለው የሃሳብ ሩጫ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱስ አጋልጦ አጋንንት፣ የወደቁ መላዕክት፣
ኔፊሊም ያላቸውን በአዲስ የስጦታ ወረቀት ጠቅልሎ የሰው ልጅ እንዲቀበላቸው ለማድረግ የሚደረግ ሙከራ ነው። በርግጥ እነዚህን
ALIENS፣ SPACE TRAVELLERS, EXTRA TERRESTRIAL INTELLIGENCE የሚባሉትን ነገሮች እውነተኛ ምስጢር
ሁሉም ሳይንቲስት፣ ተመራማሪ ወይም ጋዜጠኛ እና የታሪክ አዋቂ ነኝ ባዩ ሁሉ ያውቃል ማለት አይደለም። እንደሌሎቹም ብዙ የእውቀት
መስኮች ሁሉ አውቀው የተደበቁ መሪዎችና ሳያውቁ ተታልለው የሚከተሉ ጀሌዎችም አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ግን እነዚህ እነሱ በተለያየ ዘመናዊና
ሳይንስ መሰል ስሞች የሚጠሯቸው ማን መሆናቸውን በብዙ ማስረጃና በግልጽ ያስረዳል። በዘፍጥረት ምዕራፍ 6 ቁጥር 1 እስከ 4 ድረስ
እንዲህ ይላል፤
“እንዲህም ሆነ ሰዎች በምድር ላይ መብዛት በጀመሩ ጊዜ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው፥
የእግዚአብሔር ልጆችም የሰውን ሲቶች ልጆች መልካሞች እንደሆኑ አዩ፣ ከመረጡአቸውም ሁሉ ሚስቶችን ለራሳቸው ወሰዱ። እግዚአብሔርም፥
መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም እርሱ ሥጋ ነውና፥ ዘመኖቹም
መቶ ሀያ ዓመት ይሆናሉ አለ። በእነዚያ ወራት ኔፊሊም በምድር ላይ ነበሩ ደግሞም ከዚያ በኋላ የእግዚአብሔር ልጆች የሰውን ሴቶች
ልጆች ባገቡ ጊዜ ልጆችን ወለዱላቸው እነርሱም በዱሮ ዘመን ስማቸው የታወቀ ኃያላን (በእብራይስጡ הַגִּבֹּרִ֛ים ሀጊቦሪም፣ ወይም እጅግ ግዙፍና ኃያላን የሆኑ ፍጥረታት)
ሆኑ።” ዘፍጥረት 6፤1
በዚሁ በምዕራፍ 6 ቁጥር 7 ላይ እግዚአብሔር አምላክ በምድር ላይ በነበረው ክፋትና
ዓመጽ እጅግ እንደ ተቆጣ፣ ሰውንም በመፍጠሩ እንደ ተጸጸተና የፈጠረውንም ሰውና እንስሳ ሊያጠፋ እንደወሰነ ይናገራል። ምክንያቱም
እነዚያ “የእግዚአብሔር ልጆች” የተባሉት የሰውን ልጆች ሚስቶች አድርገው ስለወሰዱ፣ ከዚህም ያልተፈቀደ ግንኙነት ውስጥ ኔፊሊም
የሚባሉት ግዙፍ የሆኑ ፍጥረታት ስለተወለዱ እና ኔፊሊም፣ ዘሮቻቸውና የተባበሩአቸው የምድር ሰዎችም ምድርን በዓመጽ ስለሞሏት ነበር። እነዚያ “የእግዚአብሔር ልጆች” የተባሉት ማን እንደሆኑ፣ ለምን ከነሱና ከሰዎች
ሴቶች ልጆች የተወለዱት ግዙፎችና ኃያላን እንደሆኑና የነሱንም ታሪክና ፍጻሜ በሚቀጥለው ትምህርት ላይ እንመለከታለን። ለአሁኑ ግን ጌታ እግዚአብሔር ምድርን በሙሉ በውኃ ያጠፋበት ምክንያት ላይ
እናተኩር። ይኽው ዘፍጥረት 6 ምክንያቱን ሲዘረዝር እንዲህ ይላል፤ 1ኛ) የሰው ክፋት በምድር ላይ በዛ 2) የሰው የልቡ ሃሳብና
ምኞት ሁል ጊዜ ፈጽሞ ክፉ ሆነ 3) ምድር (ሰዎች፣ እንስሳት፣ ተክሎች፣ መሬቱና ሌሎችም ግኡዛን ፍጥረታት) ተበላሸች 4)ምድር
ግፍን ተሞላች 5) ስጋን የለበሰ ሁሉ መንገዱን አበላሽቶ ነበር። እነዚህ ኃጢዓቶች ከጥፋት ውኃ በፊትና ዛሬም በሰው ልጆች
ከሚፈጸሙት በደሎች ሁሉ በዓይነትና በመጠንም እጅግ የከፉና በዘመኑ የነበረውን የሰውን ዘር ሁሉ ያካተቱ እንጂ በአንድ ወይም በጥቂት
አካባቢዎች ብቻ በተወሰኑ ሰዎች የተፈጸሙ አልነበሩም።
መጽሐፍ ቅዱስ የጥፋት ውኃ ሆነ ባለበት ዘመን (በግምት በ 2348 ዓመተ ዓለም)
አካባቢ በምድር ሁሉ ላይ በውሃ ጠፍተውና በደለል ተሸፍነው የነበሩ ቦታዎች፣ በኔፊሊም የተሰሩ ግዙፍ ስራዎችና አጽሞችም ሳይቀር
በዝቅተኛ፣ በተራራማና በከፍተኛ ቦታዎችም (plateaus) ላይ ሳይቀር ተገኝተዋል፣ እየተገኙም ነው። ባጭሩ ለማስቀመጥ ኔፊሊምና
ህገ ወጥ አባቶቻቸው (የወደቁት መላዕክት) ነበሩ ለሰው ልጅ የጦርነትና የመገዳደልን መሳሪያዎችና ተንኮልን፣ ህገወጥና ከተፈጥሮ
ባህርይ ውጭ የሆነ ፍትወተ ሥጋን፣ ልቅ የሆነ ዓለማዊነትንና ዘማዊነትን፣
ገደብ የለሽ የገንዘብ፣ የስልጣንና የዝና ስግብግብነትን እና ሌሎች እስከዛሬ ድረስ የሰው ልጅን እየፈጁና እያፋጁ ያሉ ክፋቶችን
ያስተማሩት። የወንድና የሴት ሰዶማዊነትን፣ በሰውና በእንስሳት መካከል የሚደረግ ርኩስ ፍትወተ ስጋን እና ለመናገርም እንኳን የሚዘገንኑ
ሌሎች ርኩሰቶችን ያስተማሩ እነዚህ ኔፊሊም የተባሉ እኩይ ፍጥረታትና ዘሮቻቸው ነበሩ። በማህጸን ውስጥ ጽንስን መግደልን፣ የሰውንና
የእንስሳን ዘር በማደባለቅ አስፈሪ፣ አደገኛና ዘግናኝ የሆኑ ፍጥረታትን ማስወለድ፣ ሰዎች ከአምላክ ይልቅ እነሱን ራሳቸውን (ኔፊሊምንና
ዘሮቻቸውን) እንዲያመልኩ ማድረግ፣ ህጻናት ልጆቻቸውንና ትልልቆችንም ሰዎች ለነሱ (ለኔፊሊም ገዥዎቹ) መስዋእት እንዲሰውላቸው ማድረግን
ያስተማሩ እነዚሁ የወደቁት መላእክትና ልጆቻቸው ናቸው። ከዚህም አልፈው ከሰውና ከእንስሳት እንዲሁም ከራሳቸው ከኔፊሊምና ከተለያዩ
እንስሳት ዘር የተደባለቁ ግማሽ ሰውና ግማሽ እንስሳ ፍጥረታት እንዲፈጠሩ በማድረግ የእግዚአብሔርን የተፈጥሮ ስርዓት በሙሉ ሊያጠፉት
ተቃርበው ነበር። ከኖህና ከቤተሰቡ ከእርሱም ጋር ወደመርከብ ከገቡት እንስሳት በስተቀር የቀሩቱ የምድር ፍጥረት በሙሉ በኔፊሊም
ዘርና በነሱም የረከሰ የኑሮ ዘይቤ የተበከሉና የዓመጻውም ተካፋዮች ነበሩ። ሐዋርያው ጴጥሮስ የኖህን ዘመን የወደቁ መላእክት አመጽና
ውጤቱን እንዲህ ሲል ገልጾታል:
“እግዚአብሔር ኃጢዓትን ላደረጉ መላዕክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጉድጓድ
ለፍርድ ቀን ሊጠበቁ አሳልፎ ከሰጣቸው፣ ለቀደመውም ዓለም ሳይራራ ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን አድኖ በኃጢዓተኞች
ዓለም ላይ የጥፋትን ውኃ ካወረደ>>>” 2ኛ ጴጥሮስ 2፤4 እስከ 5
የይሁዳ መልእክት ደግሞ የወደቁት መላእክት፣ የልጆቻቸው የኔፊሊም እና የተባበራቸውም
የኖህ ዘመን ዓለም የሰሩትን ታላቅ ኃጢዓት እንደሚከተለው ገልጾታል፤
“መኖሪያቸውንም የተውትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም
እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርስ ድረስ ጠብቆአቸዋል። እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ
ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘላለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል።” ይሁዳ ቁጥር 7 እና 8።
ይህንን ክፍል ስናነብ ቢያንስ የሚከተሉትን ነጥቦች እናስተውል። በኖህ ዘመን የወደቁት
መላእክት ሌላ ሥጋን (የሰውን ሴቶች ልጆችን) ተከትለው የተከለከለ ግብረ ስጋ ግንኙነትን ፈጽመው ነበር። ሰዶምና ገሞራም የጠፉበት
ኃጢዓትም እንዲሁ በሰዎች ወንዶችና ወንዶች ወይም በሶዎች ሴቶችና ሴቶች መካከል የተፈጸመ ዝሙት ብቻ ሳይሆን በወደቁ መላእክት፣
በዘሮቻቸው በኔፊሊምና በሰዎች እንዲሁም በእንስሳት መካከል የተደረጉ እጅግ ክፉ ዓመጻዎችም ነበሩ ማለት ነው።
ዘፍጥረት 6 “የእግዚአብሔር ልጆች” የሚላቸው እነማንን ነው?
መላእክት እንደሰው ሰውነት አላቸው ወይ? ኔፊሊም ለምን ግዙፍና ኃይለኛ ሆኑ? ኃይለኛ ማለት ምን ማለት ነው? ዛሬ በዓለማችን አስደናቂ
ከሚባሉ የጥንት ስራዎች ጋር ኔፊሊም ግንኙነት አላቸው ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች በሚቀጥለው ትምህርት 5 ላይ እንመለከታለን። አዘጋጅና አቅራቢ ዶ/ር በፈቃዱ ብርሃኑ አድማሱ
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ