የመለከት ጥሪ ለመንፈሳዊ ጦርነት

የመለከት ጥሪ ለመንፈሳዊ ጦርነት

ባለፈው መልዕክቴ ላይ ባጭሩ እንደጠቀስኩት ከማንኛውም የድምጽ ወይም የሙዚቃ መሳሪያ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መለከት ለብዙ አገልግሎት ሲውል እናየዋለን። ታዲ መለከት ሲነፋ ሁል ጊዜ ትርጉምና መልዕክት አለው። የእግዚአብሔር ሕዝብ ደስ ሲለውና ድል ሲያደርግ ለምስጋናና ለአምልኮ መለከት ይነፋል። በብሉይ ኪዳን ዘመን በኢየሩሳሌም በሚገኘው በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ በየእለቱ መስዋዕት በሚቀርብበት ጊዜ መለከት ይነፋ ነበር። ጌታ አምላክ ራሱ ነው ሙሴ ቢያንስ ሁለት የብር መለከቶችን እንዲሰራ ያዘዘው። መለከት መቼ፣ ለምን እና እንዴት እንደሚነፋም በዝርዝር ትዕዛዝን ለሙሴ የሰጠው ጌታ ራሱ ነበር። ይህም በኦሪት ዘኈልቁ ምእራፍ 10 ከቁጥር 1 እስከ 10 ድረስ ተጽፎልናል። ዛሬ እንድናተኩርበት የምሻው የመለከት አገልግሎት ግን እኛ እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ ከኤደን ገነት ጀምሮ በዓለማችን ላይ እየተካሄደ ያለውን መንፈሳዊ ጦርነት እንዳንዘነጋና ነቅተንም እንድንዋጋ ለመቀስቀስ ነው። የመለከት አገልግሎት በብሉይ ኪዳን የቆመ ነገር አይደለም። በደስታና በድል ጊዜአችን በመለከት፣ በበገና፣ በመሰንቆ፣ በከበሮና በሌሎችም መሳሪያዎች ጌታን ማምለካችንና መዘመራችን መልካም ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልሶ እስኪመጣ ድረስ ግን የግድ መንፈሳዊ ጦርነቶች አሉብን። ሓዋርያው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 14፤8 ላይ ወደጦርነት የሚቀሰቅስ የመለከት ድምጽ እንዳለ አስተምሮአል። በ2ኛ ሳሙኤል 2;28 ላይ ደግሞ ጦርነትን ለማቆምም መለከት እንደሚነፋ እንማራለን። የክርስቲያን ጦርነት በዚህ ዓለም ካሉት ጦርነቶች ሁሉ እጅግ ከባድ፣ የመዋጊያ መሳሪያዎቹም የተለዩ እና መንፈሳዊ መሆነቸውንም ይኽው ሓዋርያ በ 2ኛ ቆሮንቶስ ምዕ 10 ቁጥር 3 እስከ 6 ድረስ ተጽፎልናል። የምንጋደለው በመንፈሳዊ ስፍራ ከሚገኙ፣ ነገር ግን ይህንን እኛ የምንኖርበትን ቁስ አካላዊ ዓለምም ሊበጠብጡ እና የሰውን ዘር ለማጥፋት ከሚዋጉ የጨለማው ዓለም አለቆች፣ ከሥልጣናት፣ ከገዢዎችና የክፋት መንፈሳውያን ሰራዊት ጋር ነው። ኤፌሶን 6፤10 እስከ 20። በዚህ ጦርነት ውስጥ እያንዳንዳችን የመዋጋት ግዴታ አለብን። ያለን ምርጫ ጠላትን መዋጋት ወይም እጅ ሰጥተን የጠላት መጫወቻ መሆን ነው። በጸጋ ድነናልና መዋጋት ምን ያስፈልጋል የሚል ክርስቲያን የወንጌል መልእክት አልገባውም። አዎን በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው በክርስቶስ የዳንነው። ነገር ግን ያው ያዳነን ጌታ ደግሞ በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ብሎናል። መስቀሉንም ተሸክመን እንድንከተለው ጠርቶናል። ከጦርነቶቻችን አንዱ ለምድራችንና ለምንኖርበት አገር እንዲሁም ምድርን ለሚመሩት የታላላቆቹ አገሮች መሪዎች መጸለይ ነው። ሌሎች ክርስቲያን መሪዎች ስለ አገራችን ስለ ኢትዮጵያ እንድንጸልይ አሳስበውን ስንጸልይ ቆይተናል። ዛሬ ደግሞ ስለ ታላላቆቹ የምድር መንግስታት፣ በተለይም ደግሞ ስለ አሜሪክ እንድንጸልይ በጥብቅ አሳስባችኋለሁ። በፊታችን ያለው ጊዜ ምድር እጅግ ወደ ትልቅ አደጋ እየተፋጠነች ያለችበት ወቅት ነው። የአሜሪካ ምርጫ አለፈና አንድ ወገኑ አሸነፈ ቢባልም፣ ከዚሁ ከምርጫው ጋር ከተያያዙ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ አገሪቱ ገና አልወጣችም። ለአሜሪካ እንጸልይ። መቼም የኣሜሪካ ክፉ ነገር ውስጥ መውደቅ ምድርን ሁሉ፣ እኛንም ሁላችንን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እንደሚጎዳ የምንክድ አይመስለኝም። በሚቀጥሉት ሳምንታትና ወራት የሚደረገው የስልጣን ሽግግር ሰላማዊ እንዳይሆን የሚቀሰቅሱ ብዙ ጥሪዎችና ጥረቶች መኖራቸውን ሁኔታውን በቅርብ የሚከታተሉ ባለሙያዎችና መሪዎች እያስጠነቀቁ ነው። ለአሜሪካ እንጸልይ።  ባለፉት ጥቂት አመታት ዓለማችን በተፋጠነና በሚያስፈራ ሁኔታ ወደ ጦርነት እየተገፋች ነው። የሮማው ሊቃነ ጳጳስ ፍራንሲስ ደጋግመው ሲናገሩ በምድር ላይ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት በትንሽ በትንሹ ጀምሮአል ብለዋል። እጅግ ታላላቅና አስፈሪ የሆኑ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የቱርክ፣ የሩሲያ፣ የቻይና፣ የኢራን፣ የሰሚንና የደቡብ ኮሪያ የጦር ሃይሎች በሰሜንና በምስራቅ አውሮፓ፣ በጥቁር ባህር፣ በሜዲትራኒያን ባህር፣ በኢራንና አካባቢው በሚገኘው የፋርሱ ባህረ ሰላጤ ፣ በደቡብ የቻይና ባህር፣ በኮሪያ ባህረ ሰላጤ ዙሪያ ሰፍረዋል። ብጥብጥ፣ ጦርነትና እልቂትን ጌታ አምላክ አልፈጠረም ይህም ፈቃዱ አይደለም። አሁን ምድርን የሚያሰጋት ደግሞ እጅግ የሚያስፈራ የኑክሊየር  ጦርነት ነው ። የኑክሊየር ጦርነት ማለት ምን እንደሆነ አብዛኛው የሰው ዘር አያውቅም። ወገኖች ስለዚህ ለመጻፍ አሁን ቦታ አይበቃኝም። ነገር ግን ይህንን የመለከት ጥሪ እንስማ። በገና እና በአዲስ አመት ዋዜማ ለምን ስለዚህ ዓይነት ነገር ትናገራለህ ብትሉኝ ይገባኛል። ገናን እናክብር። አዲስ አመትንም በተስፋ እንቀበል። ነገር ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ደግሞ ዘመኑን እንድንለይና በምድር ሁሉ ላይ አንዣቦ ስላለው ጥቁር ደመና እንድንጸልይ ይህንን የመለከት ድምጽ እንዳሰማ ግድ ይለኛል። ለአሜሪካ፣ ለካናዳ፣ ለሌሎቹም ታላላቅ መንግስታትና ለአገራችንም ኢትዮጵያ እንጸልይ። እኛ የክርስቶስ ነን። በህይወትም ሆነ በሞት የምንፈራው ነገር የለም። ነገር ግን ጌታን ላላወቁትና ለዘላለም ሊጠፉ ላሉት ህዝብ ሁሉ እንዲጸልይ ከኛ ይልቅ ጌታ ማንን ይጥራ? የዛሬው የመለከት ድምጽ ይህ ነው።  እንጸልይ !!

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

ሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ የምድርን አየር እያናጋ ነው፣ የምድር መንቀጥቀጥና እሳተ ገሞራም የማፈንዳት ጥፋቶች ይሰራሉ

በኖኅ ዘመን እንደነበረው የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ክዶ ራሱ አምላክ ለመሆን ሲቃጣው በራሱ እና በእግዚአብሔር ፍጥረት ላይ ትልቅ ጥፋትን እየፈጠረ ነው። ዶ/ር በፈቃዱ አድማሱ ጌታ አምላክ የሰው ልጅ ሊ...